በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊኖር እንደሚችል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው እና መንግሥት ‘ሸኔ’ ከሚለው ታጣቂ ቡድን ጋር የሚደረግ ሦስተኛ ድርድር “ወደ ሰላም ለመምጣት ወይም እስከ መጨረሻው ላለመነገጋር” የሚወሰንበት የመጨረሻ ንግግር ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ታንዛኒያ ዛንዚባር ውስጥ እንዲሁም በዚህ ዓመት፣ ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ ያደረጓቸው ሁለት ዙር ንግግሮች ያለውጤት መጠናቀቃቸው ይታወሳል።

ኢታማዦር ሹሙ ለኤፍ ቢሲ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ፣ ካለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ እስከ ኅዳር 11 ድረስ፣ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም የተደረገው ሁለተኛው ዙር ድርድር ላለመሳካቱ ምክንያት ያሏቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ ኩምሳ ድሪባን እና ሌሎች የጦሩ አዛዦች፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ፊት ለፊት የተገናኙበት ሁለተኛው ዙር ድርድር “በስምምነት ይቋጫል” የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ፈጥሮ ነበር።

ድርድሩ ከተጀመረ ከቀናት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ ንግግሩን መቀላቀላቸውም በጥሩ ምልክትነት ተወስዶ ነበር።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑም ድርድሩ “በጥሩ ሁኔታ” እየተካሄደ እንደነበር የተናገሩ ሲሆን፣ በሁለቱ አካላት መካከል አለመስማማትን የፈጠሩ ጉዳዮች የተነሱት መጨረሻ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢታማዦር ሹሙ አለመግባባት አምጥተዋል ካሏቸው “ዝርዝር ጉዳዮች” መካከል በቀዳሚነት የጠቀሱት “ሥልጣን አካፍሉኝ” በሚል ቀርቧል ያሉትን ጥያቄ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ይህንን ጥያቄ ያቀረበው የራሱን “ፕሮፖዛል” አዘጋጅቶ መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “መሠረታዊ ልዩነት የፈጠረውን” ይህንን ጥያቄ መንግሥት እንዳልተቀበለው ተናግረዋል።

ታህሳስ 03 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *