በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመምህራንን ደሞዝ ለአፈር ማዳበሪያ ዉዝፍ ዕዳ በመዋሉ መምህራኑ ለከፍተኛ ችግር ተማሪዎቹ ደግሞ ከትምህርት ገበታ ዉጪ መሆናቸዉ ተነገረ

የወረዳዉ መምህራን ደሞዝ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ መቋቁም የማይችሉት የኑሮ ጫና ውስጥ እንደሚገኙ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በልዩ ዞኑ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፤ትምህርት በማቆማቸው በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ም ሰምተናል፡፡

ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዝ እየተቆራረጠ ከመከፈሉ የተነሳ ኑሮን እጅጉን እንዳከበደባቸው ቅሬታቸዉን አሰምተዋል፡፡

አሁን ግን የማዳበሪያ ዕዳ መከፈል አለበት በሚል ደሞዝ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ህይዎታቸዉን መምራት እስኪያቅታቸው ድረስ በመቸገራቸውና ስራ ማቆማቸውን መምህራኑ ገልጸዋል፡፡

በአዲሱ በማዕከላዊ ደቡብ ክልል በከምባታ ዞን ስር በምትገኘው በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ውስጥ ያሉ መምእራን የፌደራሉ መንግስት ትኩረት እንዲሰጣቸው ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ወር በላይ ደሞዝ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ፤ከራሳቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር ወደ ማይችሉበት ሆኔታ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በተደጋጋሚ ወደ ልዩ ወረዳው ፤ወደ ዞኑ፤እና ወደ ክልል አመራሮች ድረስ ብናመራም ፤መፍትሄ የሚሰጠን አካል አጥተናል ያሉት መምህራኑ፤ ቅሬታቸውን ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቢሮ እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤምም ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የደወለ ሲሆን ከመሬት ማዳበሪያ ዕዳ የተነሳ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ መክፈል እንዳልቻለ ወረዳው አስታውቋል፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ አፍሪጦ ከወረዳው አደረጃጀት በፊት የነበሩ የማዳበሪያ እዳ ውዝፎች ለዚህ ፈተና እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡
እንደዛም ሆኖ ጤናው እና የትምህርቱ ዘርፉ መጎዳት የለበትም በሚል ለጤና ባለሞያዎች እና ለመምህራን የጥቅምት ወር 17 በመቶ ደሞዝ መከፈሉን አስተዳደሩ ገልጸዋል፡፡

ከደሞዝ አለመከፈል ጋር በተገናኘ ከትምህርት ስርዓቱ ውጭ ያሉ ትምህርት ቤቶች በመኖራቸው በወረዳ አቅም የምንችለውን እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

በመሳይ ገብረ መድህን
ታህሳስ 09 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.