በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ77 ሺህ በላይ አዳዲስ ሰዎች በካንሰር እንደሚያዙ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ 52 በመቶ የሚሆነው ሞት ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች እንደሚከሰትም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከሚከሰተው 52 በመቶ ሞት ደግሞ 7 በመቶው የሚሆነው በካንሰር ህመም የሚከሰት መሆኑንም የጤና ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጄ ድጉማ ገልፀዋል።

የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘው የኦሶፋጃል/የጉሮሮ/ ካንሰር መሆኑም ተነስቷል።

በአገራችን በጉሮሮ ካንሰር ከሚጠቁ አጠቃላይ ሰዎች መካከልም 68 በመቶ የሚሆኑት የሚገኙት ከኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ባሌ መሆናቸውም ተገልጿል።

በወንዶች ላይ ከፕሮስቴት ካንሰር ቀጥሎ ሁለተኛው ገዳይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በሴቶች ላይ ደግሞ ከጡት እና ማህፀን ጫፍ ካንሰር ቀጥሎ በማጥቃት በሶስተኛነት ተቀምጧል።

በጉሮሮ ካንሰር ከተጠቁ ሰዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱ ናቸውም ተብሏል።

በህመሙ ከተያዙ ሰዎች መካከልም 15 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ህክምና የሚያገኙት።

የጉሮሮ ካንሰር ህመም ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ዶ/ር ደረጄ ነገር ግን አሁንም በገዳይነቱ ቀጥሏል ነው ያሉት።

ጤና ሚኒስቴርም ለ5 ዓመታት የሚቀጥል የካንሰር መከላከል ስትራቴጂ ዕቅድ ነድፎ በክልሎችም ውስጥ እየሰራበት እንደሚገኝ አንስተዋል።

አገራችን የካንሰር ህመምን የማከም አቅም አላደበረችም ያሉት ሚኒስትር ድኤታው፤ መከላከል ላይ ትኩረት አድርገን መስራት አለብን ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የበሽታው አስከፊነት ከመጨመሩ የተነሳ የካንሰር መድሃኒት አሁን ላይ ከህይወት አድን መድሃኒቶች ውስጥ ተካቷል ነው ያሉት።

በአገራችን ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች እና የትራፊክ አደጋ ትልቁ ፈተና እንደሆኑም ተነስቷል።

በዛሬው ዕለትም ጤና ሚኒስቴር ፣ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፣ የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፣ የነጌሌ አርሲ ሆስፒታል እና የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የጉሮሮ ካንሰርን ለመከላከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በእስከዳር ግርማ

ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.