ኢትዮ ቴሌኮም ለ3.6 ሚሊየን ሰዎች የብድር አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ኩባንያዉ በዲጂታል የብድር አገልግሎቱ ለ3.6 ሚሊየን ደንበኞቹ ብድር መስጠቱን ነዉ የገለጸዉ፡፡

ከዳሽን ባንክ እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ባቀረባቸዉ የብድር አገልግሎቶቹ ከ3.6 ሚሊየን በላይ ሰዎች ብድር ማግኘታቸዉን ገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ የተሰኘ ባንኮች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ኢንሹራንሶች እና ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት አገልግሎታቸዉን ለተጠቃሚዎች ማድረስ የሚችሉበትን የፋይናንስ አገልግሎት ስርዓት ዘርግቷል፡፡

በዚህ ስርዓት አማካኝነትም የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከ40 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የቴሌብር ደንበኞች ማድረስ ይቻላል መባሉን ካፒታል ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

ኩባንያዉ እንደገለጸዉ ከሆነ ይህ ስርዓት የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የብድር፣ የቁጠባ እና የኢንሹራንስ አገልግሎታቸዉን አንድ በሆነዉ የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ላይ ለደንበኞቻቸዉ ማቅረብ የሚችሉበት ሲሆን፤ተጠቃሚዎችም ከየትኛዉም ቦታ ሆነዉ በእጅ ስልኮቻቸዉ ብቻ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ፡፡

የሚሰጠዉ የብድር አገልግሎት የደንበኞችን የብድር ታሪክ ፣ ያለፈ ብድርን በጊዜዉ የመመለስ ታሪክ እና ሰዉ ሰራሽ አስተዉሎትን በመጠቀም ያለምንም ማስያዣ የሚሰጥ አገልግሎት ነዉ፡፡

በተጨማሪም ኩባንያዉ ያስተዋወቀዉ የዲጂታል አክሲዮን ግዢና ሽያጭ የፋይናንስ አገልግሎት ፍቃድ ያላቸዉ የቢዝነስ ተቋማት የአክሲዮን ሽያጫቸዉን ዲጂታላይዝ በማድረግ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ለብዙዎች መድረስ የሚችሉበት መሆኑም ነዉ የተገለጸዉ፡፡

በእስከዳር ግርማ
ታህሳስ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.