በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ ቢሆኑም በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ችግር እንደፈጠረባቸው በድጋሜ አስታወቁ

በአማራ ክልል የሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎች በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለነባር እንዲሁም አዲስ ለተመደቡ ተማሪዎቻቸው ጥሪ ሳያደርጉ አራት ወራት ተቆጥረዋል።

ተማሪዎችም ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመድባቸውና ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጉትጎታ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ግን በአማራ ክልል የሚገኙ አስሩም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ጠርተው ትምህርት እንዲያስቀጥሉ እንደተነገራቸው እና ተቋማቱም በቅርቡ ጥሪ ለማድረግ መስማማታቸውን ይናገራል።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮ ኤፍ ኤም ትምህርት መቼ ለመጀመር እንዳሰቡ በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ጊዜያዊ ፀሀፊ የሆኑት ዶክተር ንጉስ ታደሰን ጠይቋል ።

አስር ዩኒቨርሲቲዎችን በአባልነት የያዘው በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ጊዜያዊ ፀሀፊ የሆኑት ዶክተር ንጉስ ታደሰ በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ተማሪዎችን መጥራት እንዳላስቻላቸው አንስተዋል።

ተቋማቱ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ያነሱት ፀሐፊው በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ግን እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልፀዋል።

በአማራ ክልል የሚገኙ የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንና የፀጥታው ሁኔታ የበለጠ ሲሻሻል ለተማሪዎቻቸው ጥሪ እንደሚያደርጉ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል።

ለአለም አሰፋ

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ታህሳስ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.