ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ ትልቅ ነገር ቢሆንም ጎረቤት ሀገራትን በማያስቆጣ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እዉቅና ትሰጣለች መባሉም ከሶማሊያ ጋር ሊያቃቅር እንደሚችልም ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ጥቅም ከሚያስገኙ መሠረተ ልማቶቿ ለሶማሊላንድ ድርሻ ከመስጠት በተጨማሪ ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷ እየነገረ ነዉ፡

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችዉ ስምምነት ሊኖረዉ የሚችለዉ ተስፋና ስጋት እንዲሁም ስምምነቱ በአለም አቀፍ እንዴት ይታያል ስንል የህግ ባለሙያ ጠይቀናል፡፡

በጂግጂጋ ዩንቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ ሰለሞን ጓዴ ስምምነቱ የባህር በር ጥያቄዉ በየት በኩል የሚለዉን ምላሽ ሰጥቷል ባይ ናቸዉ፡፡
ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ በኩል የባህር በር እንደምታገኝ በነገሩ ነዉ፡፡

ሶማሊላንድ እ.አ.አ 1991 ራሷን ከሶማሊያ በመገንጠል ነጻነቷን ብታውጅም ኢትዮጵያን ጨምሮ የትኛውም አገር እስካሁን ዕውቅና ሳይሰጣት ቆይቷል።

ይሁን እንጅ የመግባቢያ ሰነዱ ይህን እንደሚቀይር የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ለሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊላንድ በይፋ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር ትሆናለች ብለዋል።

አቶ ሰለሞን ይህ ከአለም አቀፍ ህግ አንጻር በተለይም ከቬናዉ ኮኔቬንሽን ጋር የሚጠረስና ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስጋት እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን ተከትሎ ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ ለምትመለከታት ሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠት ሊያስቆጣት ይችላል የሚሉ ሃሳቦች ሲነሱ ነበር።

ሞቃዲሾም አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በአዲስ አበባ የሚገኘኙትን አምባሳደሯን ጠርታለች ተብሏል፡፡

ይህ ደግሞ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለዉን ግንኙነት ሊያበላሽ እንደሚችል የህግ ባለሙያዉ ስጋታቸዉን ያነሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ የባህር ማግኘቷ ተገቢ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ሰለሞን ነገር ግን የወደብ ጥያቄን በሰከነና በበሳሰ የዲፕሎማሲ ጥበብ ማስኬድ ካልተቻለ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ግጭት ሊስገባን ይችላል፡፡

እናም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይግድ ይላል ብለዋል፡፡ እናም ከሶማሊያ ጋር ያለን ግንኙነት እንዳይበላሽ መሰራት አለባት ነዉ የተባለዉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ስምምነቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ የመግባቢያ ሰነዱ ኢትዮጵያ የባሕር በርን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ መንገዱን ይጠርጋል ብሏል።

ስምምነቱ የሁለቱን መንግሥታት የጸጥታ፣ ኢኮኖሚ፣ እና የፖለቲካ አጋርነት እንደሚያጠናክር አንስቷል።

በነበረው የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ላይም የጠቅላይ ሚንስትሩ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ ለምታገኘው የባሕር በር በምላሹ ለሶማሊላንድ ከቴሌ ወይም ከአየር መንገዱ ድርሻ ልታገኝ እንደምትችል ተናግረዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በቴሌኮምም ይሁን፤ በአየር መንገድ ጥቅም የሚያስገኙ መሠረተ ልማቶች ድርሻ ለመስጠት የሚያስችል ዕድል አለው ሲሉ ሶማሊላንድ ከመግባቢያ ሰነዱ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም ጠቆም አድርገዋል።

ሶማሊላንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎችም አገራት ይፋዊ ዕውቅና ያልተሰጣት ራስ ገዝ አገር ስትሆን፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው ስምምነት ውስጥ ስለ ሶማሊያ ዕውቅና የተጠቀሰ ነገር የለም።

ሶላሚላንድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘትም እየተጣጣረች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ፋላጎቷን ለማሳካት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን ሬድዋን አንስተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን የመግባቢያ ሰነድ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመው ሰጥቶ መቀበል በሚል መርህ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በምላሹ ጦር ሰፈር መገንባት እና ወደብ ማልማት የሚያሰችላትን የባሕር ጠረፍ እንደምታገኝ አብራርተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን የመግባቢያ ሰነዱ በ50 ዓመት የሚታደስ የጦር ሠፈር ለመገንባት እና የባሕር ንግድ ለማከናወን ወደብ ማልማት የሚያስችል የባሕር ጠረፍ የሊዝ ስምምነት እንደያዘ ተናግረዋል።

መንግስት የመግባቢያ ስምምነቱን ዝርዝር በቀጣይ እንደሚሳዉቅ ቢገልፅም ኢትዮጵያን የባሕር በር ያስገኝላታል የተባለው ስምምነት የፈረመችው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻን ሰጥታ 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ስለመሆኑ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡

በአባቱ መረቀ
ታህሳስ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.