በአዲስ አበባ ናፍጣ ለማግኘት ተቸግረናል….  አሽከርካሪዎች።

ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ አሽከርካሪዎች ነዳጅ ፍለጋ ከተማውን በሙሉ እያሰሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በበርካታ የነዳጅ ማደያዎች ናፍጣ እንደሌለ የተናገሩት አሽከርካሪዎች ከትላንት ሌሊት ጀምሮ ወረፋ እንደያዙ ገልጸዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም በከተማው የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለማረጋገጥ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ቅኝት አድርጓል።

ቅኝት ካደረገባቸው አካባቢዎች መካከል ከቦሌ አንስቶ እስከ ፒያሳ፣ ከመገናኛ ጎሮ፣ ከፒያሳ ቃሊቲ መስመር ከፒያሳ ሜክሲኮ እንደዚሁም ከፒያሳ አስኮ ባሉት ማደያ ጣበያዎች  ይገኙበታል።

ጣበያችን በቅኝቱ እንደተመለከተው ናፍጣ የሚገኘው በተወሰኑ ማደያዎች ውስጥ መሆኑን ታዝቧል።

የነዳጅ ማደያዎች ባሉባቸው ቦታዎች ሊገለጽ በሚከብድ መልኩ ከሌሊት 9:00 ሰአት ጀምረው የተሰለፉ አሽከርካሪዎች ምሽቱን አሳልፈው እስካሁን ድረስ መሰለፋቸውን ተመልክቷል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም ያነጋገራቸው ሹፌሮች እንደተናገሩት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባናውቅም በነዳጅ ምክንያት ስራ ፈተን እየተንከራተትን ነው ብለዋል።

ናፍጣ የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች ከተማዋን በረጃጅም ሰልፎች አጨናንቀውት ይገኛሉ።

ናፍጣ ባለባቸው ማደያዎች የቀዱ አሽከርካሪዎች ናፍጣ ከመጥፋቱ ውጪ የዋጋ ለውጥ አለመኖሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ ባለስልጣን እና የነዳጅ አቅራቢዎች ማህበር በጉዳዩ ዙርያ ለማነጋገር ስልክ የደወልን ቢሆንም ልናገኛቸው አልቻልንም።

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *