ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለሦስተኛ ጊዜ ለመሙላት ማቀዷን ተከትሎ የግብፅ ፕሬዝደንት አል ሲሲ ስጋታቸው ማየሉን ተናግረዋል፡፡

የግብፅ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ የግብፅ የውሃ ድርሻን ‘ማንም ሀገር ሊሻማው አይችልም ‘ ብለዋል ሲል ሚድል ኢስት ዓይ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ በበኩሏ ሶስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በመጪው ነሃሴ ለማስጀመር ማቀዷን ሰሙኑን ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ቀደም ፕሬዝደንቱ በአንድ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው አገራቸው የአባይ ውሃ ድርሻዋን ለማሳደግ ስትል ከአፍሪካ መንግስታት ጋር ግጭት ውስጥ እንደማትገባ ተናግረው ነበር፡፡

ቀደም ሲል በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያን ወክለዉ ይደራደሩ የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ከአዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ማይክ ሃመር ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በአባይ ግድብ ጉዳይ ላይ የሦስትዮሽ ዉይይትን ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት መግለፃቸዉን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባሳለፍነው ዓርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ አምባሳደር ኢ/ር ስለሺ በቀለ የተናገሩትን በማስረገጥ «ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ሕብረት የሚመራዉን የሦስትዮሽ የህዳሴ ግድብ ዉይይትን ለመቀጠል ፍላጎት አላት» ብሏል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን እና ግብፅ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ለተደጋጋሚ ጊዜ ያካሄዱት የሦስትዮሽ ድርድር ያለዉጤት መጠናቀቁ ይታወቃል።
ባለፈዉ የካቲት ወር ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በከፊል የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ማስታወቋም አይዘነጋም።

በያይኔአበባ ሻምበል

ሰኔ 08 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *