አሜሪካ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም ኃይሎች “የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሷን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ።

በምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች፤ የአማራ ኃይሎች “የዘር ማጽዳት” እና “በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል” መፈጸማቸውንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረው አስታውቀዋል።

ብሊንከን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን በተመለከተ ሀገራቸው የደረሰችበትን መደምደሚያ ያስታወቁት፤ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሀገራት በ2022 የነበረውን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ የሰነደ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓመታዊ ሪፖርት ትናንት ይፋ ሲደረግ ነው።

ይህ የአሜሪካ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ሪፖርት፤ በስድስት ጎራ የተከፋፈሉ 198 አገሮች እና ግዛቶችን የተመለከተ ነው።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪፖርቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ በኢራን፣ አፍጋኒስታን፣ በርማ፣ ቻይና እና ኩባ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ቢጠቃቅሱም፤ ሰፊ ጊዜ የሰጡት ግን የኢትዮጵያን ጉዳይ ነበር።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች ፈጽመውታል ያለው ድምዳሜ ላይ የደረሰው፤ “ሕጉን እና እውነታውን በጥንቃቄ ካጠና በኋላ” መሆኑን በመግለጫቸው መጥቀሳቸውን የኢትዮጵያን ኢንሳይደር ዘገባ ያመለክታል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች እና የአማራ ኃይሎች፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሼያለሁ” ሲሉ ብሊንከን በዚሁ መግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ኃይሎች፤ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች እና ማሰቃየትን ጨምሮ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ፈጽመዋል” ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *