ፓርቲው በኢትዮጵያ እስልምና እምነት ተከታዮች አና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስላሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ አውጥቷል፡፡
አብያተ እምነቶቻችን አይነኬ የእሴቶቻችን መሠረቶች ናቸው ሲል እናት ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ
መንግስት “የሸገር ከተማ” ብሎ በሰየመው አካባቢ የሚኖሩ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዉያንን የማፅዳት ዘመቻ ሃይ ባይ ሳይኖረው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ቤት አልባና ተመጽዋች አድርጓቸዋል ሲል ነው የገለጸው ፓርቲው።
ላባቸዉን አንጠፍጥፈዉ ከሰሩት ቤት በማፈናቀል በማን አለብኝነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እየተፈጸመባቸው ይገኛል ብሏል፡፡
ይህ እዉነታ መንግሥት ሕዝብን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ከመምራትና ከማስተዳደር ይልቅ፣ በሕዝብ መከራና ሰቆቃ መሳለቅን መገለጫው አድርጎ ለመቀጠሉ ትልቅ ማሳያ ነው ሲል አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ መንደርና ከተማ መስርቶ በሚኖርበት አካባቢ ሁሉ ለሥጋዊ ፍላጎቱ መሟላት ከሚያደርገዉ ሩጫ አስቀድሞ መንፈሳዊ አገልግሎቱን የሚያገኝበትና የሚያከናዉንበት አብያተ እምነት ግንባታ ግንባር ቀደም ሥራዉ ነዉ ብሏል በመግለጫው፡፡
‘’የሸገር ከተማ‘’ ግንባታም እስካሁን በተከናወነው የማፍረስ ሥራ ሕዝበ ሙስሊሙ የሚገለገልበትን 19 መስጂዶች እንዲፈርሱ አድርጓል ብሏል፡፡
በመስጅዶች መፍረስ ምክንያት ሕዝበ ሙስሊሙ ተቃዉሞዉን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ በወጣበት የዓርብ የጁምዓ ሶላት ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ ብዙዎች ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ሲሆን ባለን መረጃም ሦስት ሰዎች ሕይወታቸዉ አልፏል ነው ያለው፡፡
በተመሳሳይ ወቅት በአርሲ ሀገረ ስብከት በጢዮ ወረዳ በጨፌ ሚሶማ ቀበሌ ገበሬ ማኀበር ከአሰላ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኘው በዴራ አማኑኤል አጥቢያ ቤተክርስቲያን ላይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ካህናትና ምዕመናን፤ በታጣቂዎች በተሰነዘረ ጥቃት ዘግናኝ ጭፍጨፋና ግድያ ተፈጽሞባቸዋል ብሏል።
በሚያሳዝን ሁኔታ ህዝባችን በመንግሥት ቸልተኝነት ሞትን በየእለቱ እንዲለማመድ ተፈርዶበታል ብሏል፡፡
እናት ፓርቲ የእምነት ተቋማት ማኅበረሰባችንን አጽንተዉ ያቆሙ የማንነታችን መገለጫ ናቸውም ሲል ገልጾ፡ በመንግሥትና በታጣቂ ቡድን የተፈጸመዉን እርምጃም በጽኑ እንደሚወግዝም ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በ”ሸገር ከተማ” ስም እያከናወነ ያለዉን አፍራሽ ተግባር በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል፡፡
ፓርቲው ለደረሱ ውድመቶችና መፈናቀሎች ተጠያቂነት እንዲኖርም ጠይቋል፡፡
ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም
