የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከሚቀጥለው በጀት አመት ጀምሮ ከእዚህ ቀደም በወረቀት አማካይነት ይፈጸም የነበረውን የግዢ ስርዓትን ሙሉ ለሙሉ በዲጅታል አሰራር እንደሚተካ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እስከ ሐምሌ 1 / 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ፣ 95 የፌደራል ተቋማት ወደ ኤሌክትሮኑክስ የግዥ ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የተቋሙ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አበበ አለሙ ተናግረዋል፡፡
አስቀድመው ወደዚህ የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት ውስጥ ከገቡ 74 ተቋማትን ጨምሮ አዲሶቹ ሲታከሉበት 169 የፌደራል ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት ብቻ እንዲስተናገዱ ይደረጋ ተብሏል፡፡
ከፌደራል ተቋማቱ በተጨማሪ በአሁን ወቅት በአዲሱ የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት ውስጥ የገቡትን 9 ሺህ 252 አቅራቢዎችን ቁጥር ወደ 30 ሺህ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በወረቀት አማካይነት ይደረጉ የነበሩ የግዥ ክንውኖች ለብልሹ አሰራር እና ለሃብት ብክነት ሲዳርጉ እንደነበር አቶ አበበ ነግረውናል።
በረድኤት ገበየሁ
ሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም
