በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኝው አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክስዮን ማህበር፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ እንዲሁም መካከለኛ የንግድ ተቋማትን ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን “ስማርት ሶሉሽን” የተባለ ቴክኖሎጂ ነው በዛሬው እለት ይፋ ያደረገው፡፡
“ስማርት ሶሉሽን ለስማርት ሰዎች” በሚል ይፋ ያደረገው ይህ ስርአት ተቋማት በቀላሉ ባሉበት ቦታ ሆነው ስራቸውን እና ገቢያቸውን የሚቆጣጠሩበት ቴክኖሎጂ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡
የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል በቀለ እንደተናገሩት፣ በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ተቋማት ዌብሳይት በራሳቸው ማበልጸግ የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋቱን ገልጸው፣ ከዜጎች የሚጠበቀው ከድርጅቱ ጋር ስምምነት ማደረግ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትጠቀማቸው አብዛኛዎቹ የቴክኖጂ ውጤቶች ከቻይና እና ከህንድ የመጡ ናቸው ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ይህም በመሆኑ ቴክኖሎጂው የውጭ ምንዛሬን የሚቀርፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በመነቃቃት ላይ የሚገኘውን የዲጂታል ዘርፍ ለማዘመንና በመንግስት እስከ 2025 ድረስ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ላይ የግል ሴክተሩ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ይጫወታልም ብለዋል፡፡
አሸዋ ቴክኖሎጂ በኦንላይን ግብይት ፤ በሎጂስቲክስ ፤ ደሊቨሪ እንዲሁም ስማርት ቴክ ሶሉሽን ደንበኞችን አፍርቶ አምራች ነጋዴዎች፤ በጊዜ እና በቦታ ሳይገደቡ ተደራሽ የሚሆኑበትን ምቹ የግብይት መድረክ ፈጥሮ በስራ ላይ ይገኛል ተብሏል።
ድርጅቱ አሁን ላይ በአስራ አንድ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ የከፍተኛ በጀት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም
