የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በሱዳን ስላለዉ ግጭት እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በካይሮ መነጋገራቸዉን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
የሁለቱ አገራት መሪዎች ዉይይት የሱዳን የጎረቤት አገራት መሪዎች በሱዳኑ ግጭት መፍትሄ ዙሪያ ከሚያደርጉት ጉባኤ በፊት የተደረገ መሆኑንም የዜና ወኪሉ አክሎ ጠቅሷል፡፡
በግብጽ ፕሬዝዳንት በኩል የወጣ መግለጫ እንደሚያሳየዉ ሁለቱ መሪዎች በሱዳን ያለዉን ግጭት ማቆም በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ፣ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ እና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ መነጋገራቸዉን ያሳያል፡፡
ግብጽ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከአባይ ወንዝ ከምታገኘዉ የዉሃ መጠን አብላጫዉን ድርሻ ይወስዳል በሚል እንደ ቋሚ ስጋት የምትቆጥረዉ ሲሆን፣ በግድቡ አሞላል እና አሰራር ዙሪያ አሳሪ ስምምነት እንዲኖር ትፈልጋለች፡፡
ኢትዮጵያ በበኩሏ ግድቡ ለምታደርገዉ የዕድገት ጉዞ ወሳኝ መንገድ መሆኑን በማንሳት ፣ የታችኛዉ ተፋሰስ አገራት የሆኑትን ግብጽን እና ሱዳንን የዉሃ ድርሻ በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይጎዳ ትገልጻለች ሲል ዜና ወኪሉ አክሏል፡፡
ለዓመታት በግድቡ አሞላል እና አሰራር ዙሪያ ሲደረግ የነበረዉ ዉይይት መፍትሄ ማምጣት አለመቻሉንም ገልጿል፡፡
ዕሮብ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ የሱዳን የጎረቤት አገራት መሪዎች ጉባኤን የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ልኡካንን መርተዉ ወደ ግብጽ ሄደዋል፡፡
ሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ እና በመንግስት ጦር መካከል ከሚያዚያ ጀምሮ በተፈጠረ ግጭት እስካሁን 3ሺህ ንጹሃን የተገደሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መጎዳታቸዉ የአናዶሉ ኤጀንሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በእስከዳር ግርማ
ሐምሌ 06 ቀን 2015 ዓ.ም
