በሀገሪቱ ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር ቢኖርም መንግስት ላለፉት አመታት በየአመቱ 6 በመቶ ለሆኑት ብቻ የስራ እድል እንደሚፈጥር አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የማክሮ ኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ መንግስት ላለፉት በርካታ አመታት 2.4 ሚሊየን ወይም ከስራ ፈላጊው ህዝብ መካከል 6 በመቶውን ብቻ ሲቀጥር መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ከዚህም የተነሳ በርካታ ተመራቂ ተማሪዎች ለስራ አጥነት ችግር እና ለስነ-ልቦና ቀውስ መዳረጋቸውን አንስተዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በጥናታቸውም ፤የሃገሪቱ የእድገት ምንጭ የሆነው በአብዛኛው የስራ እድል የማይቀጥረው ሴክተር መሆኑን ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛው ቀጣሪ ዘርፍ ግብርና ነው ያሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ 35 በመቶውን የሚሸፍነው ደግሞ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በራሱ ስራን ፈጥሮ የሚያኖረው ግለሰብ ነው ብለዋል፡፡
የሃገሪቱ የእድገት ምንጭ እና ስራን መፍጠር የሚችለው የኢኮኖሚ ክፍል የተጣጣመ አለመሆኑ፣ ሃገራችን ላይ እየተስተዋለ ለሚገኘው ከፍተኛ ስራ አጥነት ዋና ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር አለማየሁ የአግሮ ኢንደስትሪ እና የማኒፋክቸሪንግ ዘርፉ በሃገሪቱ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋእጾ ቢኖራቸውም፣ በእነርሱ ላይ በበቂ ሁኔታ ኢንቨስት አልተደረገም ይላሉ፡፡
ስራ መፍጠር የሚችለው የኢኮኖሚ ክፍል የእድገት ምንጫችን ቢሆን ኖሮ፣ የስራ አጥነቱን መጠን ማቅለል እንደሚቻል የጥናታቸው ውጤት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡
በመሳይ ገ/መድህን
ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም
