የቀድሞ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ኢምራን ካን ክስ ተመስርቶባቸው የሞት ፍርድ ሊፈረድባቸው እንደሚችል አርቲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ክስ ላይ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት አለ በሚል በርካቶች ተቃውሞ ሲያሰሙ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
በፓኪስታን የሚገኘው ልዩ ፍርድ ቤት የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ካን እና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የነበሩት የመንግስትን ሚስጥራዊ ህግ ጥሰዋል በሚል ነው ክስ የመሰረተባቸው፡፡
ካን ባለፈው አመት በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ከስልጣን እንዲወርዱ የተደረጉት በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በተቀነባበረ ሴራ ነበረ መባሉን መረጃው አመላክቷል፡፡
ክሱ በዋናነት የሚያጠነጥነው አግባብ ባልሆነ መንገድ በስልጣን ላይ መቆየታቸውን እና የመንግስትን ሚስጥራዊ ሰነድ ለህዝብ ይፋ በማድረጋቸው ነው ተብሏል፡፡
የክስ ሂደቱን የሚመሩት የፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግ ኡመር ኒያዚ እንዳሉት፣ የመንግስት ሚስጥሮችን የማውጣቱ ክስ ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት ቅጣት የሚያደርስ ነው፡፡
ኢምራን ካንም በዚህ ክስ ጥፋተኝነታቸው የሚረጋገጥ ከሆነ እስከ ሞት የሚደርስ ፍርድ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡
በመሳይ ገ/መድህን
ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም
