በዓለም ዙሪያ ከመኖሪያ ቤታቸዉ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ114 ሚሊዮን በላይ እንደሚገመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትላትናዉ ዕለት ባወጣዉ ሪፖርት አስታውቋል።
እ.ኤ.አ በ2023 አጋማሽ አንስቶ በዩክሬን፣በሱዳን፣በማንያማር እና ኮንጎ ሪፐብሊክ የነበሩ ግጭቶች እንዲሁም በአፍጋኒስታን ዉስጥ ያለዉ የተራዘመ የሰብዓዊ ቀውስ እና ድርቅ በሶማሊያ ያለዉ የፀጥታ ሁኔታ የተፈናቃዩን ቁጥር እንደጨመረዉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ በመግለጫው አስታዉሷል።
“በአለም አቀፍ ደረጃ በጦርነት፣በስደት እና በሰብዓዊ መበት ረገጣ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በሴፕቴምበር መጨረሻ ከ114 ሚሊዮን ሊበልጥ ይችላል” ሲል ኤጀንሲዉ ገልፃል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ሃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ እንዳሉት “በአሁን ሰዓት የዓለም ትኩረት ሁሉ በጋዛ ላይ ነዉ ነገር ግን በአለም አቀፍ ደረጃ እጀግ በጣም በርካታ ግጭቶች እየተበራከቱ የንፁሀን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል” ብለዋል።
ሃላፊዉ አክለዉም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ግጭቶችን መፍታት አለመቻሉን በመጥቀስ ግጭቶችን ለማስቆምና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መኖሪያቸዉ እንዲመለሱ ትብብር እንዲደረግ ማሳሰባቸዉን የዘገበዉ ፍራንስ 24 ነዉ።
በአቤል ደጀኔ
ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም
