በሃገራችን የሚገኙ ባንኮች የሚያስጀምሯቸው አዳዲስ የዲጅታል ቴክኖሎጂዎች ህዝብን መዝረፊያ መንገዶች ናቸው ይላሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች፡፡
አብዛኛው የሃገራችን ባንኮች የሞባይል ባንኪንግን ጨምሮ እንደ አዲስ የሚያስጀሯቸው የዲጅታል ቴክኖሎጂዎች ከህዝብ የባንክ አካውንት ብርን መቁረጫ መንገዶች ሆነዋል ባይ ናቸው ተጠቃሚዎቹ፡፡
በሃገራችን በዲጅታል ግብይት ስርዓት ላይ አብዛኛው የሃገራችን ማህበረሰብ ያለው ንቃተ ህሊና በጣም አነስተኛ ስለመሆኑ የባንክ ባለሞያዎች በየጊዜው ሲያነሱ ይሰማል፡፡
ለዚህ ደግሞ እንደ ዋና ምክንያት የሚያነሱት፣ ባንኮች በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ላይ ፤ለማህበረሰቡ አስቀድሞ ግንዛቤን ከማስጨበጥ ይልቅ፣ የሚፈጠረውን የዲጅታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በምን አይነት መንገድ ከህዝቡ ገቢን አገኛለሁ ብለው ማሰባቸው እንደሆነ ነው፡፡
አስቀድሞ ግን በማህበረሰቡ ላይ ስለጉዳዩ ሰፊ ግንዛቤን መፈጠር መቻል፤ለዘላቂ እና አዋጭ ቢዝነስ ትልቅ አቅም እንዳለው ያነሳሉ፡፡
የ27 ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ እንዲሁም የባንክ ባለሞያ የሆኑት አቶ አስቻለው ታምሩ፣ አዳዲስ የባንክ ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሙ ደንበኞች በባንኮች ሊበረታቱ እንጂ ብር ተቆራጭ ሊሆንባቸው ባልተገባ ነበር ይላሉ፡፡
ለዚህ ምክንያት ብለው ያነሱት ደግሞ የዲጂታል ባንኩን የሚጠቀሙ ሰዎች ፤ ባንኮችን ከቅርንጫፍ ኪራይ ፤ከሰው ሃይል እና ከተለያዩ ወጪዎች መታደግ መቻላቸውን ነው፡፡
ስለዚህ የባንክ ቴክኖሎጂን ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞች በባንኮች ሊበረታቱ እንጂ፤ቴክኖሎጂውን ስለተጠቀሙ ከባንክ አካውንቶቻቸው ላይ ገንዘብ ተቆራጫ ሊሆን እንደማይገባ አቶ አስቻለው ተናግረዋል፡፡
ብዙ ጊዜ ባንኮች ከዚህ ጋር ተያይዞ በባንክ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት የህዝብን ጊዜ መቆጠብ መቻላቸውን እና ኑሯቸውን ማቅለላቸውን ምክንያት በማድረግ ከህዝቡ አካውንት እንደአጠቀቀማቸው መጠን ገንዘብ ተቆራጭ እንደሚሆን ያነሳሉ፡፡
ከዚህ ይልቅ ደንበኛው ገንዘብ ተቆራጭ ሊሆንበት ይገባ የነበረው የባንክ ቅርንጫፎች በአካል ሄዶ በመጠቀሙ እንጂ፤ቴክኖሎጂውን በመገልገሉ አልነበረም ብለዋል፡፡
አክለውም የሃገራችን አብዛኛው ባንኮች በሚያስጀምሯቸው አዳዲስ የዲጅታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂዎች ፤አስቀድመው ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማይሰጡ ናቸው፡፡
ስለሆነም ሃገራችን በ2025 አሳካለሁ ብላ የያዘችውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ እቅዷን እንድታሳካ ካስፈለገ፣ ባንኮችን ጨምሮ የተለያዩ የቢዝነስ እና የመንግስት ተቋማት ግንዛቤን አስቀድሞ በመፍጠር ከቴክኖሎጂ ጋር እኩል የሚጓዝ ትውልድን መስራት እንደሚኖርባቸው ባለሞያው አንስተዋል፡፡
ማህበረሰቡ ላይ ቀድመን የምንፈጥራቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ካሉ ፤የዲጅታል ቴክኖሎጂው ግኝት የግብይት እንቅስቃሴውን ፤አሰልቺ እና ውስብስብ እንዳይሆን ያደርገዋል ተብሏል፡፡
ይህ ካልሆነ ግን ከሚፈጠረው አዲስ ቴክኖሎጂ እኩል የሚራመድ ማህበረሰብ ከሌለ፤ የግብይት ስርዓቱን አሰልቺ ከማድረጉም ባለፈ፤እንደ ሀገር ውጤታማ የመሆን እድላችንን ያጠበዋል ሲሉ የባንክ ባለሞያው አቶ አስቻለው ታምሩ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጸዋል፡፡
በመሳይ ገ/መድህን
ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
