ረቂቅ ህጉ ክልሎችም የገጠር መሬትን የሚያስተዳድር ተቋም እንዲያቋቁሙ ያስገድዳል፡፡
በረቂቅ አዋጁ እንደተብራራው አርሶና አርብቶ አደሮች ከመሬታቸው ያለ መፈናቀል መብታቸውን ማስከበር አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት፣ በመሬት የመጠቀም መብትን በማስያዝ ብድር ማግኘት እንዲችሉ ከአገሪቱ የመሬት ፖሊሲ ጋር በማጣጣም በጥንቃቄ ታስቦ የተዘጋጀ አዋጅ ነው ተብሏል፡፡
የገጠር መሬትን ዋስትና አድርጎ ማስያዝን የሚመለከት የሕግ ድንጋጌ እስካሁን አለመኖሩ በረቂቁ ተመላቷል፡፡
የገጠር መሬት ባለቤት የመጠቀም መብቱን በየክልሉ በሚወጡ ሕጎች በሚወሰን የጊዜ ገደብ አማካይነት፣ ለፋይናንስ ተቋማት ለብድር ዋስታና ማስያዝ እንደሚቻል ተገልጿል፡፡
ባለይዞታዎች በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸውን በማስያዝ፣ የዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችና ግብዓቶችን የሚያገኙበት አሠራር ማመቻቸትን ያለመ ስለመሆኑ በረቂቁ ተብራርቷል፡፡
አበዳሪዎች ሕጋዊ የፋይናነስ ተቋማት ብቻ ሲሆኑ፣ አራጣ አበዳሪነትን ለመከላከል ግለሰቦች በሕጉ መሠረት አበዳሪ ሆነው በመሬት የመጠቀም መብትን እንደ ማስያዣ ሊይዙ እንደማይችሉ በረቂቁ መደንገጉን የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል፡፡
ግብዓት ለመግዛት የገንዘብ እጥረት የሚያጋጥማቸው መሬታቸውን ያከራዩ ወይም ያስጠምዱ የነበሩ ባለይዞታዎች፣ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን በማስያዝ ብድር ወስደው አምርተው ብድራቸውን እንዲመልሱ የሚያስችል መብት ስለመሆኑም በረቂቁ ተጠቁሟል፡፡
ድንጋጌው ከዚህ በፊት የብድርና ቁጠባ ተቋማት የሚሰጡትን ብድር የሚተካ ሳይሆን እንደ አማራጭ የመጣ ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ህዳር 03 ቀን 2016 ዓ.ም
