“ታጣቂዎች ያለ ምክንያት ጫካ አይገቡም፤የሰው ደም አይፍሰስ፤ልዩነቶች ወደ ውይይት መድረክ ይምጡ”—ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አራዓያ ታጣቂዎች ያለምክንያት ጫካ እንደማይገቡ ጠቅሰው የሰው ደም ሳይፈስ፣ አጀንዳዎች ወደ ምክክር እንዲመጡ ጠይቀዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ የተቋማቸውን የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ አራት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ ‹‹እኛ የሰላምን ጥያቄ ነጥለን ታጣቂዎችን ፕሪቶሪያ ወይም ዛንዚባር ወስደን እንዲነጋሩ የምናደርግበት ዘዴ የለንም፣ ነገር ግን እናበረታታለን›› ብለው፣ ምክር ቤቱ አስፈጻሚው ላይ ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ጉልበት ያላችሁ እናንተ ናችሁ፤ ስለዚህ ወደ ሰላም ኑ፣ መንግሥትም ሆድህን አስፋ ተቀባይ ሁን፣ እናንተም ትጥቃችሁን አስቀምጣችሁ ወደዚህ ኑ፣ የሚለውን ነገር ከእኛ ይልቅ ጉልበትና አቅም ያላችሁ እናንተ ናችሁ፤›› በሚል ለፓርላማው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

‹‹የትም አገር የተካሄደ ውጊያ መጨረሻው ውይይት በመሆኑ፣ ከመተላለቃችንና ከመጨፋጨፋችን በፊት አሁንም አልመሸም፣ ይህ ጉዳይ በምክር ቤቱ ፊት ሊተላለፍ ይገባል ፣ ወደ ምክክር እንምጣ ›› የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአንዳንድ ክልሎች ነፍጥ ካነሱ አካላት ጋር የጀመረው ጥረት ካለ ተብሎ የተጠየቀውን ጥያቄ ሲመልሱ፣ እነዚህን አካላት በምክክር ሒደቱ ለማካተት ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማነጋገርና እነዚህ አካላትንም በተወካይ ለማነጋገር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ህዳር 03 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *