በሃዋሳ ቅርንጫፍ ብቻ ያልተሰበሰበ የ1 መቶ 41 ሚሊየን ብር ዕዳ መኖሩንም ሰምተናል፡፡
ጤና ተቋማት በዱቤ መድሃኒት ይወስዳሉ ነገርግን ብድራቸዉን በጊዜ አይመልሱም ይሄም ከፍተኛ ችግር እየፈጠረብን ነዉ ሲሉ የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሰ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ተቋማት ዕዳ ስላለባቸዉ አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችን ቢፈልጉ እንኳን ወደ እኛ የመምጣት ነገር የለም ያሉት አቶ ዘመን፤ህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያደርሱ መድሃኒቶች ሲሆኑ ዕዳም እያለባቸዉ የምንሰጥበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ ሲሉ ነግረዉናል፡፡
ምክንያቱም እኛ መድሃኒት አንሰጥም ብለን ብንከለክል ህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ችግር ነዉ የሚፈጠረዉ ብለዋል፡፡
በብድር ለሚወስዱ የጤና ተቋማት የመክፈያ የጊዜ ገደብ እንሰጣለን ያሉት ስራ አስኪያጁ ፤የበጀት ጫና ያለባቸዉ ጤና ተቋማት ላይ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ከበጀት መዳቢዉ አካል ጋር መነጋገር ጀምረናል ብለዉናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ተጠያቂ መሆን ያለባቸዉ ጤና ተቋማት ይጠየቃሉ ያሉም ሲሆን ፤በፍርድ ቤት የክስ ሂደት ላይ ያሉ መኖራቸዉን ገልጸዉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዉ እየከፈሉ ያሉ ስለመኖራቸዉም ነዉ የተናገሩት፡፡
ከጤና ተቋማት ጋር ያለን የስራ ግንኙነት መበላሸት ስለሌለበት የክስ ሂደቱን የመጨረሻ አማራጭ አድርገን ነዉ የምንወስደዉ ያሉት አቶ ዘመን፤ መሰብሰብ ያለበት የገንዘብ መጠን ግን ከፍተኛ በመሆኑ ችግር አስከትሎብናል ብለዉናል፡፡
ተቋሙ ለትርፍ የተቋቋመ ባለመሆኑ ፤ጠንካራ የመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለት እንዲኖር ከተፈለገ ጠንካራ ፋይናንስ ያስፈልጋል ሲሉም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 01 ቀን 2016 ዓ.ም
