በአዲስ አበባ መሥሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ብሔር ያላቸው አመራሮች ብዛት ከ40 በመቶ እንዳይበልጥ ሊደረግ ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚኖሩ ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች መካከል ተመሳሳይ የብሔር ማንነት ያላቸው አመራሮች ብዛት ከ40 በመቶ እንዳይበልጥ ሊያደርግ መሆኑ ታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ ለሚተገብረው የሠራተኞች ድልድል ሲባል ከ14 ሺህ በላይ የከተማ አስተደደሩ ሠራተኞች ነገ አርብ ታኅሣሥ 12/2016 ዓ.ም. ለፈተና እንደሚቀመጡ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ገልጿል።

163 ሺህ ገደማ ሠራተኞች በስሩ ያሉት የከተማ አስተዳደሩ፤ በሚተገበረው ለውጥ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የከተማዋን የመንግሥት ሠራተኞችን በአዲስ መልኩ መደልደል የሚለው ይገኝበታል።

በመጀመሪያው ዙር ይህ ድልድል እንዲተገበርባቸው የተመረጡት የከተማ አስተዳደሩ 16 ተቋማት ናቸው።

ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር፣ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር፣ ትራንስፖርት፣ ፐብሊክ ሰርቨሲ እና ሰው ሀብት ልማት፣ ፕላን እና ልማት፣ ሥራ እና ክህሎት፣ እንዲሁም ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮዎች ይገኙበታል።

ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች የከተማይቱ ኤጀንሲዎች እና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ድልድሉ ከሚተገበርባቸው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተካትተዋል።

እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ድልድል የሚደረግባቸው በማዕከል ቢሮዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ላይ ባሉ ጽህፈት ቤቶቻቸው ጭምር ነው።

የቢሮ ኃላፊው፤ የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ፈተና ለመስጠት ያቀደው የሠራተኞቹን “የብቃት ደረጃ ለማረጋገጥ” እንደሆነ ገልጸዋል።

ፈተናው የባህሪ እና የቴክኒክ ምዘናዎች እንደያዘ የገለጹት ዶ/ር ጣሰው፤ “የሚሰጠው የቴክኒክ ምዘና [ሠራተኞቹ] ከሚሠሩት ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ነው። የባህሪው [ፈተና] ደግሞ አገልግሎት አሰጣጡን የሚፈታተኑ የባህሪ ችግሮች ስላሉ ያንን ክፍተት ለመሙላት አመላካች እንዲሆን ተስቦ የተዘጋጀ ነው” ሲሉ የፈተናውን ይዘት አብራርተዋል።

ኃላፊው፤ ምዘናው በአዲስ አበባ እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ መዘጋጀቱን የገለጹ ሲሆን፣ ፈተናው የሚሰጠውም በዩኒቨርስቲ ወይም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው መረጃም ነገ አርብ ታኅሣሥ 12/2016 ዓ.ም. ፈተናውን የሚወስዱ ሠራተኞች ቁጥር ከ14 ሺህ በላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የሪፎርም ሥልጠና ሰነዱ እንደሚያስረዳው የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች ፈተናውን ለማለፍ ከ50 በመቶ በላይ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። “ከዚህ [የማለፊያ ውጤት] በታች [የሆነ] ነጥብ ያገኘ ባለሙያ ከደረጃው ዝቅ ብሎ ባሉት የአስተዳደር እርከኖች” ላይ እንደሚመደብ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

ለዳይሬክተሮች እና ለቡድን መሪዎች የተቀመጠው የፈተና ማለፊያ ነጥብ ደግሞ 60 በመቶ ሲሆን፤ ይህንን ነጥብ የማያስመዘግቡ አመራሮች ለዳይሬክተርነት ወይም ለቡድን መሪነት ኃላፊነት መወዳደር እንደማይችሉ ሰነዱ ማስቀመጡን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።

ይሁንና ይህ የአመራሮች ድልድል “የብሔር ብሔረሰብ ስብጥርን ባካተተ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ” እንደሚከናወን ይገልጻል። ሰነዱ አክሎም፤ “በመሥሪያ ቤቱ ካሉ የሥራ መደቦች [መካከል] በተመሳሳይ ማንነት የተያዙት ከ40 በመቶ መብለጥ የለባቸውም” ሲል ይህንን ድልድል በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ባጸደቀው ደንብ ላይ የተቀመጠውን አሰራር ያስረዳል።

መሥሪያ ቤቶቹ ድልድሉን ሲያከናውኑ ይህንንን የብሔር ስብጥሩን ለመጠበቅ እንዲችሉ “ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች በመለየት በዝውውር እንዲሟሉ” እንደሚደረግም በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ታህሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *