ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ገዢው ፓርቲ ድርጅታዊ ስራውን ከመንግስት መዋቅር እንዲለይ ጠየቀ
ነእፓ የፓርቲ አባል ያልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች በብልጽግና ፓርቲ ስልጠና እንዲሳተፉ የሚደረግበት አሰራር እንዲቆም ጠየቀ።
ድርጅቱ ትላንት ሰኞ ታህሳስ 29 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ “በግብር ከፋዩ ገንዘብ የፓርቲ ስልጠና ማካሄድ” ኢ-ህገ መንግስታዊ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።
“የፓርቲ አባል ያልሆኑ የፌዴራል እና የክልል የመንግስት ሰራተኞች የገዢውን ፓርቲ ስልጠና እንዲወስዱ ማድረግም ሆነ የፓርቲ ስልጠናን በመንግስት በጀት ማካሄድ ህገ መንግስቱን እና አዋጃ ቁጥር 1162/2011 የሚቃረን በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላት ድርጊቱን ለማስቆም አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ” ሲል ነእፓ ጠይቋል።
ፓርቲው ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኝ ለሲቭል ሰርቪስ ኮሚሽን እና ሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከያቸው አካላት ጥያቄ ማቀረቡን አክሎ ገልጿል።
ታህሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም
