የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር ወደ ካምፓላ እና አዲስ አበባ ይጓዛሉ ብሏል በመግለጫው ።
አምባሳደር ሃመር በካምፓላ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እና በሱዳን ላይ በሚያተኩረው 42ኛው የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ ብሏል ።
ዩናይትድ ስቴትስ ይህን የኢጋድን ዲፕሎማሲያዊ ተነሳሽነት በደስታ እንደምትቀበለው ባወጣችው መግለጫ አሳውቃለች፡፡
አሜሪካ በአውሮፓውያኑ “1960 የድንበር ወሰን መሠረት አሜሪካ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ዕውቅና ትሰጣለች” ሲል በመግለጫው አትቷል፡፡
አምባሳደር ሐመር ከካምፓላ በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያቀኑ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
በኡጋንዳ መዲና ዛሬ የሚካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ከያዛቸው ሁለት መወያያ ርዕሶች አንደኛው በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ነው።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አባል በሆኑበት በኢጋድ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ “በጊዜ መጣበብ” ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች መሳተፍ እንደማይችሉ መግለጹ እየተነገረ ነው።
በአፍሪቃ ቀንድ እና በአካባቢው የግጭት ስጋት ያስከተለው ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያ “ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው” በማለት ተቃውሞዋን አሰምታለች።
ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመስጠት በምላሹ ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ለማግኘት ነው በመሪዎቻቸው ፊርማቸውን ያኖሩት።
ኢጋድ ይህን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ስብሰባ መጥራቱን ያወደሰችው አሜሪካ ተወካይዋ አምባሳደር ሐመር ምክክሩን እንዲታደሙ መላኳ አሳውቃለች፡፡
አምባሳደር ሀመር በተጨማሪም ከአንድ ዓመት በፊት በስምምነት የተቋጨውን የትግራይ ጦርነት ተከትሎ የሚከናወነውን ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ተሃድሶ እና ማሰናበትን በተመለከተ እንዲሁም ተጎጂዎችን መሠረት ስላደረገው የሽግግር ፍትህ ሂደት ጋር ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያወሉ ተብሏል።
አምባሳደር ሀመር በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚስተዋሉ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውሶችን ለመፍታት ውይይት እንዲደረግ አሳስበዋል።
ጥር 09 ቀን 2016 ዓ.ም
