ከ700 በላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት ደሞዝ አልተከፈለንም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

ከ700 በላይ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጅ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከሁለት ዓመት በላይ ደሞዝ አልተከፈለንም ሲሉ ለመቀሌ ቅርንጫፍ እንባ ጠባቂ ተቋም ቅሬታ ማስገባታቸውን ሰምተናል፡፡

የመቀሌ ቅርንጫፍ እንባ ጠባቂ የስራ ኃላፊ ጸሓዬ አንባዬ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በትግራይ ክልል ጦርነቱ መቀስቀሱን ተከትሎ የትግራይ ክልል ተቋማትን እንዲጠብቁ ወደ ትግራይ ክልል የተላኩ ከ700 በላይ የሚሆኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ደሞዛቸው እንደተቋረጠ እና ተበታትነው እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ኃላፊው ለጉዳዩ የምርመራ ቡድን ተቋቋሞ እና ጉዳያቸውን የመመርመር ስራ በዋናው የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም በኩል እንደታየም አንስተዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ የፌድራል መንግስት መቀሌ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ የትግራይ ክልል መንግስት ተቋማትን እንዲጠብቁ የተላኩ እንደሆኑም ተነስቷል።

የፌድራል አባላቶቹ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም የህወሓት ሀይሎች ዳግም መቀሌን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ደግሞ ደሞዛቸው እንደተቋረጠ አቶ ፀሀዬ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ በኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መጠየቁን ተከትሎ በሰጠው ምላሽ ደሞዝ ያልተከፈለበት ምክንያት የተወሰኑ አባላት የተቋሙን ደንብና ህግ ባለማክበራቸው እንዲሁም የተቀሩት በጡረታ በመገለላቸው ነው ሲል ምላሽ መስጠቱን ጣብያችን ካገኘው የመልስ ደብዳቤ መረዳት ይቻላል፡፡

ለዓለም አሰፋ

የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *