ሴቶች በግጭት እና በጦርነት ተፈናቅለው ባሉበት አካባቢ ፆታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሚገኝም ከሚኒስትሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከጣቢያችን ኢትዮ ኤፍ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስተር የሴቶች ጥቃት ጥበቃና ምላሽ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዘካርያስ ደሳለኝ፣ ካለው ሀገራዊ ሁኔታ እና ከችግሩ ውስብስብነት አንፃር የሚደረጉ ድጋፎችን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
በየቦታው ተፈናቅለው የሚገኙ ሴቶች የሚደርስባቸውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከልም ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎችን በመመደብ ስራዎችን እየሰራም እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ተፈናቅለው ለሚገኙ ሴቶች የምግብ ነክ ድጋፎችን በተለያየ ግዜያት እየሰጡ እንደሚገኙም ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ስለሆነ ከፍተኛ ጥረት እና የአሰራር ስርአት የሚጠይቅ ፖሊሲ ማዘጋጀት አስፈልጓል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ፖሊሲ የማዘጋጀት ስራዎች ተጠናቀው ለሚመለከተው አካል ተልኮ እስኪፀድቅ እየተጠበቀ እደሚገኝም አንስተዋል፡፡
ፖሊሲው ትኩረቱን ያደረገበት አንዱ ጉዳይም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሴቶች ላይ ከመፈፀማቸው አስቀድሞ ምን መሰራት አለበት የሚለውን እንዳካተተም አቶ ዘካርያስ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማም ፖሊሲው ለሴቶች ጥበቃና ከለላ የሚደግበትን ስርአትም እንደያዘም ተነግሯል፡፡
በተለያዩ ግዜያት በሚፈጠሩ ግጭቶች በዋናነት የሴቶችን ህይዎት አስቸጋሪ ያደርጋል የሚሉት አቶ ዘካሪያስ የሚመለከተው አካል ሴቶች ለሀገር አንድነት ያላቸውን ጠቃሜታ መረዳት አለባቸው ብለዋል፡፡
ስለሆነም ለሴቶች በሚደረጉ ስራዎች ላይ ተገቢው የሆነ በጀት እና የሰው ሀይል ስለሚያስፈልግ ሁሉም የሚመለከተው አካል ርብርብ ሊያደረግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሐመረ ፍሬው
የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም
