በኢትዮጵያ ያሉ የዶክተሮች ቁጥር 20ሺህ አይሞላም ተባለ፡፡

በኢትዮጵያ ህክምና ተምረዉ የተመረቁ ዶክተሮች ቁጥር ወደ 17ሺህ አከባቢ እንደሆነ ሰምተናል፡፡

ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተግባር ይግዛዉ ፤ በአገራችን ያሉ የሀኪሞች ቁጥር ወደ 17ሺህ ነዉ ያሉን ሲሆን፤ ከዚህ መሃል ወደ 40 በመቶ የሚሆነዉ ወይም 1ሶስተኛዉ ብቻ የማህበሩ አባል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዉስጥ በቂ ሃኪም የለም ያሉት ዶ/ር ተግባር፤ካለዉ የማህበረሰብ ቁጥር አንጻር በፍጹም በቂ የሀኪም ቁጥር የለንም ብለዋል፡፡

ካለዉ የህዝብ ቁጥር አንጻር ያለዉ የዶክተሮች መጠን ለ10ሺህ ሰዉ እንኳን አንድ ሃኪም የለም ማለት የሚያስችል መሆኑን ነግረዉናል፡፡

ጉዳዩን ከፍ አድርገን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ መመልከቱን ትተን በአፍሪካ ደረጃ ያለዉን ሁኔታ እንኳን ብናይ ለ10ሺህ ሰዉ በአማካይ ወደ 1.5 አከባቢ የሚደርስ ሀኪም አላቸዉ ነዉ ያሉት፡፡

የአገራችንን የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ብንወስደዉ ካለን የህዝብ ቁጥር አንጻር ዝቅተኛ ነዉ ያሉት ዶክተር ተግባር፤ቁጥሩን እንኳን ብንተወዉ ትላልቅ የሚባሉ የመንግስት ሆስፒታሎች ጭምር የምናየዉ የህዝብ መጨናነቅ የሚያሳየን ፍላጎቱ እና አቅርቦቱ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ነዉ ብለዋል፡፡

አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ይህ ቢሆንም ግን ሀኪሞች የስራ ዕድል እያገኙ አይደለም ፤ ሁሉንም ሀኪሞች እየቀጠረን አይደለም ብለዋል፡፡

የሙያ ማህበር መቅጠር አይችልም ፤ማድረግ የሚችለዉ ጉዳዩን ማሳወቅ ነዉ ያሉት ዶ/ር ተግባር፤ከጤና ሚኒስቴርም ሆነ ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር ጭምር በጉዳዩ ላይ ተነጋግረናል ብለዉናል፡፡

አሁን ላይ የተወሰኑ ለዉጦች ቢኖሩም አሁንም መፍትሄ የሚፈልጉ ብዙ ችግሮች አሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መንግስት እንዳይቀጥር የበጀት ዕጥረት መኖር ፣ የመደብ ችግር፣ ከደህንነት እና ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር በተያያዘ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች መሄድ የማይፈልጉ ባለሙያዎች መኖር ለስራ ዕጦቱ እንደ ምክንያት አንስተዋቸዋል፡፡

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 04 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *