ፖርቲዉ በመላዉ ሀገሪቱ በትጥቅ ትግል ዉስጥ የሚገኙ ቡድኖችንና መንግስትን ለማስታረቅ ማሰቡንም ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል።
የእርቅና የሰላም ጥሪዉ “ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ” የሚል ስያሜ እንደተሰጠዉ ፖርቲዉ አስታዉቋል።
ባለፉት ዓመታት የእርስበርስ ጦርነት ዉስጥ እንገኛለን የሚሉት የነፃነት እና እኩልነት ፖርቲ ሊቀምንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም ይህም ከፍተኛ ቁሳዊና ሰብዓዊ ጉዳት እያደረሰ ነዉ ሲሉ ለጣብያችን ተናግረዋል።
ይህ መቆም አለበት በሚል ተነሳሽነት ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሀይማኖት አባቶች ጋር በመሆን መንግስትንና ተፋላሚ ሀይሎችን የማስማማት ስራ እንጀምራለን ብለዋል።
በአማራ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ያሉ ተፋላሚ ሀይሎችን ወደ ዉይይት ለማስገባትም ስራ መጀመራቸዉን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም የተለያዩ የሰላም ዉይይት ጥረቶች ቢደረጉም በተለይም የመንግስት ፍቃድኝነት ባለመኖሩ ሳይሳካ መቅረቱ ይገለፃል።
የነፃነትና እና እኩልነት ፖርቲ ከዚህ ቀደም ያልተሳኩ የእርቅ ሂደቶች ቢኖርም በሀገር ጉዳይ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገራችን እየታየ ያለው የትጥቅ ትግል አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር አብዱልቃድር ጠመንጃ መፍትሄ ሊሆን አይገባም ብለዋል።
የለዉጡ መንግስት በርካታ ተስፋዎችን ይዞ ቢመጣም የታሰበዉን ያክል ባለመሆኑ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በሰላማዊ መንገድ መታገሉ ተመራጭ ነዉ ሲሉ ለጣብያችን ገልፀዋል።
አቤል ደጀኔ
መጋቢት10 ቀን 2016 ዓ.ም
