በደቡብ ትግራይ ራያ ጨርጨር አከባቢ አንድ ሰው ላይ ፖሊዮ መከሰቱን ተከትሎ ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ሰምተናል።
በመላው ትግራይ ለሚገኙ 1.9 ሚሊየን ለሆኑ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ክትባቱ ለመሰጠት መታቀዱን ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች አስተባባሪ የሆኑት አቶ መብርሃቶም ሀፍቱ ነግረውናል።
በትግራይ ክልል ባሉ አጠቃላይ 93 ወረዳዎች ላይ ክትባቱን ለመስጠት ቢታቀድም የክልሉ መንግስት የሚቆጣጠራቸው 79 አከባቢዎች በመሆናቸው በእነዚህ ስፍራዎች ላይ ክትባቱ መሰጠት ጀምሯል ነው ያሉት።
የቀሩትን እና የክልሉ መንግስት የማይቆጣጠራቸውን ስፍራዎች ደግሞ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀናል ብለውናል።

የክልሉ መንግስት በሚቆጣጠራቸው 79 አከባቢዎች ላይ ለሚገኙ 1.8 ሚሊየን ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ከሚያዚያ 15 ጀምሮ ክትባቱ እየተሰጠ ይገኛል።
ከ2መቶ ሰዎች መካከል 1መቶ 99 የሚሆኑ ሰዎች ፖሊዮ ቢኖርባቸው እራሱ ምልክት ስለማያሳዩ አንድ የፖሊዮ ታማሚ ከተገኘ ችግሩ ተከስቷል ተብሎ ነው የሚታመነው ብለዋል።
ችግሩ ወረርሺኝ ሳይሆን የፖሊዮ ክስተት ነው ያሉት አቶ መብርሃቶም ነገርግን በክትባት መቆጣጠር ስለሚቻል ወደ ሌላ ሳይዛመት ለማስቆም እየሰራን ነው ብለዋል።
ክትባቱ ከሚያዚያ 15-20 2016 ድረስ ቤት ለቤት የሚሰጥ መሆኑን ሰምተናል።
እስከዳር ግርማ
ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም
