በአከርካሪያችን እና በሁለት እግሮቻችን መሃከል ያለ ፤የታችኛዉ የወገባችንን ክፍል ከእግራችን ጋር የሚያገጣጥም እና የመራቢያ አካላት፣ ማህጸን የሽንት ፊኛን የሚሸከም አካል ነዉ፡፡
ዳሌ ላይ ከሚያጋጥሙ ጉዳቶች መካከል የዳሌ ዉልቃት /ስብራት አንዱ ነዉ፡፡
ጣቢያችን ኢትዮ ኤፍኤም 107.8 ስለ ዳሌ ዉልቃት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመገጣጠሚያዎች እና ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ከሆኑት ከዶክተር ገለታዉ ተሰማ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የዳሌ ዉልቃት/ስብራት እንዴት ይከሰታል?
- በተለያዩ አደጋዎች ይከሰታል፡፡ ከባድ ነገር እላያችን ላይ ሲወድቅ ይከሰታል፡፡
- በተለይ ደግሞ ቤት የሚያፈርሱ ሰዎች ለዚህ የበለጠ ተጋላጭ ናቸዉ፡፡
- የመኪና አደጋ ደግሞ ሌላዉ ምክንያት ነዉ፡፡
- የኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ጥንቃቄ አለመኖር፡፡
- ወደ ክፍለአገር ሲወጣ ደግሞ ከዛፍ ላይ መዉደቅ፤ ወደ ገደል መዉደቅ እንደ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
- የዳሌ ዉልቃት ሲያጋጥም ታዲያ ከሆዳችን ወደ እግራችን የሚወርዱ የተወሳሰቡ የደም ስሮች በመኖራቸዉ እና በዚህም የመድማት ሁኔታ ስለሚከሰት ብዙዎቹ በቦታዉ ህይወታቸዉ የማለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ ነዉ፡፡
- ሆዳችን ዉስጥ ሳምባ፣ጉበት ፣ ኩላሊት ፣ጣፊያ፣ አንጀታችን ላይ ጉዳት፣ የሽንት ፊኛም ሊቀደድ ይችላል፡፡
- በዚህ ሰዓት ደም በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚፈስ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል፡፡
- የዳሌዉን አቃፊ በጨርቅ መያዝ አለመቻል በሰዉነታችን ዉስጥ ያለዉ ደም ፈሶ እንዲያልቅ ማድረግ ነዉ በዚህም ህይወት የማለፍ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ነዉ ባለሙያዉ የገለጹት፡፡
- የሚያጋጥመን አደጋ የሚያስከትለዉ ዉልቃት ብቻ ሊሆን ይችላል አልያም ስብራት ሊሆን ይችላል አንዳንዴ ደግሞ ሁለቱም ሊሆኑ ይችላል፡፡
ምልክቶቹ ምንድናቸዉ?
- የማያቆም ከፍተኛ ህመም ይኖራል፡፡
- እግራቸዉ ወይም ዳሌያቸዉ አከባቢ የቅርጽ ለዉጥ ይኖራል፡፡
- እግራቸዉ ሊዞር ይችላል፡፡ የዳሌያቸዉ አቃፊም ቦታዉን ሊቀይር ይችላል፡፡
- መድማት ከዉጪ ልናይ እንችላለን፡፡ መድማት ላይኖርም ይችላል፡፡
- ከወገብ በታች ስሜት አለመሰማት/ፓራላይዝድ/ መሆን እና
- ከፍተኛ ደም ስለሚፈሳቸዉ ደግሞ እራስን መሳት እና እራስ አለማወቅ ሊኖር ይችላል፡፡
የዳሌ ዉልቃት በምን ይስተካከላል?
- የመጀመሪያዉ ወደ ጤና ተቋም መሄድ መሆኑን ባለሙያዉ ይናገራሉ፡፡
- ዳሌዉ ብዙ ጊዜ በአደጋ ምክንያት ስለሚከፈት ባገኘነዉ ጨርቅ በወገባችን ዙሪያ የላይኛዉ የእግራችን ክፍል ድረስ ማሰር አስፈላጊ ጉዳይ ነዉ፡፡
- ይህንን ማድረጋችን ደግሞ ደም በቀላሉ እንዳይደማ እና የደማዉንም እንዲረጋ ያደርገዋል፡፡
- ቀጥሎ ደግሞ የራጅ እና የሲቲ ስካን ምርመራዎች ይደረጋሉ፡፡
- ዉልቃት ከሆነ በቀላሉ ስቦ ማስገባት ይቻላል፡፡
- ዉልቃት እና ስብራት ከሆነ ግን ስብራቱ መያያዝ መቻል አለበት፡፡
- ዳሌ አከባቢም ከሆነ ብረት በማስገባት ከአከርካሪ ጋር ማገናኘት ይቻላል፡፡
- አብዛኞቹ የዳሌ ዉልቃቶች የሚታከሙ ናቸዉ የሚሉት ዶክተር ገለታዉ፤በቶሎ ወደ ጤና ተቋም ስለማይመጡ ግን ህይወታቸዉ የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ብዙ ነዉ ብለዋል፡፡
- ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ የደም መርጋት ስለሚያጋጥም እና የረጋዉ ደም ደግሞ ወደ ሳምባችን ስለሚሄድ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ህይወት ያልፋል፡፡
ህክምናዉ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?
- የዳሌ ስብራት ወሰብሰብ ያለ ህክምና የሚያስፈልገዉ መሆኑን ዶክተር ገለታዉ ይናገራሉ፡፡
- ብዙዎቹ እስከ ሶስት ወራት ድረስ በተጎዳዉ በኩል መርገጥ ላይችሉ ይችላሉ፡፡ በተለይ በሁለቱም እግራቸዉ ላይ ተከስቶ ከሆነ ደግሞ በዊልቼር ላይ ሊሆኑ ግድ ይላቸዋል፡፡
- አንዳንድ ሰዎች ደግሞ አደጋዉ እንደደረሰ ወዲያዉ መራመድ የሚጀምሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቀላል ዉልቃት ከሆነ እና ስብራት ከሌለዉ በነጋታዉ መራመድ የሚችሉ ሰዎች አሉ፡፡
- እንደ ጉዳቱ መጠን የመንቀሳቀሻ ግዜያቸዉም ረጅም እና አጭር ሊሆን ይችላል፡፡
- በጣም ጥቂት ሰዎች ግን ከዛ በላይ ጊዜ ሊወስድባቸዉ ይችላል፡፡ የዳሌ ስብራቱ ሲያጋጥም በጣም ከፍተኛ ሃይል ባለዉ አደጋ ስለሆነ ስብራቱ ከአንድ እና ሁለት በላይ ስለሚሆን ያንን ለመጠገን ጊዜ ይወስዳል፡፡
- የተለመደዉ ግን ከሶስት ወር እና ከዛ በላይ ነዉ፡፡
- ህክምናዉን ያገኙ ሰዎች ከሶስት ወር ጀምሮ መንቀሳቀስ ይጀምራሉ ሲሉ ባለሙያዉ ነግረዉናል፡፡
ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም
