የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጋዛ የሚገኝ የትኛዉም ስፍራ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም ብለዋል፡፡

ዋና ጸሀፊዉ በጋዛ የሚገኝ የትኛዉም ስፍራ ‹‹የሞት ዞን›› ሆኗል ሲሉ ነዉ የገለጹት፡፡

በጋዛ እተካሄደ ያለዉ ጦርነት እጅግ አድካሚ እና እረፍት የማይሰጥ ነዉ ያሉት ዋና ጸሀፊዉ በስፍራዉ ያለዉ ሁኔታ እጅግ እንዳሳሰባቸዉ ገልጸዋል፡፡

ጦርነቱን እያካሄዱ ያሉት አካላት አሁን ላይ ወደ ሰላም ድርድር ሊመጡ የሚገባበት ጊዜ ነዉ ያሉት ዋና ጸሀፊዉ፤ይህን እዉን ለማድረግ ማንኛዉንም ትብብር እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የጸሀፊዉ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪች ተመድ ሁሉንም አካላት በዓለምዓቀፍ የሰብዓዊ ህግ መሰረት ግዴታቸዉን እንዲያከብሩ እና ለዜጎች ደህንነት ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ተመድ እና የሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮቹ በጋራ በመሆን ከሰሜን ጋዛ ወደ ደቡብ ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች ድጋፍ ማድረግ መቀጠላቸዉን አንስተዋል፡፡

የተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ /ኦቻ/ በጋዛ የሚገኙ ዜጎች በየዕለቱ ለመፈናቀል በመገደዳቸዉ ከባድ አጣብቂኝ ዉስጥ መዉደቃቸዉን ይገልጻል፡፡

ወይ በጦርነቱ መሃል መቆየት አልያም ደግሞ ምንም ወይም ትንሽ ቦታ እና አገልግሎት ወዳላቸዉ ስፍራዎች መሸሽ ያላቸዉ አማራጭ መሆኑንም ያነሳል፡፡

በጋዛ ምንም ዓይነት ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም፡፡ ምንም መጠለያ፣ ምንም ሆስፒታል እንዲሁም ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ዞኖችም የሉም ሲል አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ለዘጠኝ ወራት ያህል በቀጠለዉ በዚህ ጦርነት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ከ38ሺህ 7መቶ በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል፡፡ ከ89ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል አናዶሉ ዘግቧል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ሐምሌ 09 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *