ግብፅ በድጋሚ ወደ ህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ስለመመለስ ለኢትዮጵያ በይፋ ያሳወቀችው ነገር እንደሌለ የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ግብጽ ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ጋር ለመወያየት ወደ ዳግም ውይይት ለመመለስ መወሰኗን በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል ማሳወቋን ዴይሊ ኒውስ ኢጅፕት የተሰኘው የግብጽ መገናኛ ብዙሀን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደገለፀው ግብፅ በድጋሚ ወደ ድርድሩ ለመመለስ የወሰነችው ኢትዮጵያ የአቋም ለውጥ አድርጋ አይደለም፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ አምሳሉ ትዛዙ ለጣቢያችን እንደተናገሩት እኛም እንደናንተ በማህበራዊ ሚዲያ ነው ያየነው፣ ይፋዊ የሆነ ነገር አልደረሰንም ብለዋል፡፡

እንደሚታወቀው ግብፅ በተለያየ ጊዜ የተለያየ መገለባበጥ ታሳያለች ያሉት አቶ አመሳሉ አሁን ምንም የምንለው ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እነሱ ቁማር ነው የሚጫወቱት፤ አላማቸው እንዳንጠቀም ነው፤ እንጂማ ምንም ጉዳት እንደማይደርስባቸው የታወቀ ነው፡፡

በሀብትህ ላይ አትጠቀም የሚል አለም አቀፍም ሆነ ተፈጥሯዊ ህግ ስለሌለ ፣ ማስቆም ስለማይችሉ፤ በተሳሰተ መረጃ፣ በማወናበድ፣ ዛቻና በጉልበት በሚመስል ሁኔታ ፣ መሄድን ነው የሚመርጡት ብለዋል፡፡

የኛ አቋም ግልፅና ግልጽ ነው፡፡ የአንድ ሀገር መንግስት የሚያደርገው ያለ ሀብቱን ተጠቅሞ ሀገሩን ማልማት ህዝቡን መጥቀም ነው፡፡ በእሱ ረገድ ለህዝባችን የሚበጀውን አቋም ይዘናል ፣እሱ አቋም አሁንም አልተቀየረም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አምሳሉ በሀገራችን ሀብት የመጠቀም ተፈጥሯዊም ህጋዊ መብትም አለን፤ ሀብታችንን ተጠቅመን የህዝባችንን የኢኮኖሚ ችግርና የልማት ጥማት የመፍታት ፍላጎት አለን ነው እያልን ያለነው፡፡

ቴክኒክ ነው፣ የነሱም የኛም አካላት በሚያደርት አስዋፅዖ ፤ በሚሰጡ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦች ችግሮች ልዩነቶች ይፈታሉ ስንል ነው የከረምነውም ብለዋል አቶ አምሳሉ፡፡

ቀድሞውንም የኛ አቋም የሶስትዮሽ የቴክኒካል ውይይት ይቀጥል የሚል ነው ያሉት አቶ አምሳሉ ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ወይም ወደ ሌላ ቦታ ወስደህ የፖለቲካ ጉዳይ የምታደርገው ነገር አይደለም ብለዋል፡፡

ለኛ በግብጽ በኩል ይፋዊ የሆነ ነገር ካለመድረሱም በተጨማሪ፤ አሁን እንደዚህ አስበው ነው፣ እንዲህ ሊያደርጉ ነው ወደዚህ ናቸው ብሎ ለመናገር ጊዜው ገና ነው፣ የሚሉት አቶ አምሳሉ ወደፊት የምናየው ቢሆንም እነሱ ግን ፍላጎታቸውን ሚዲያ ላይ አብረን እንዳየነው አድረገው ገልፀውታል ብለዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *