ድርጅቱ ከውጭ አገር የስራ ዕድል ፍለጋ በተጨማሪ ከ10 በላይ የተለያዩ አገራት ቋንቋዎችን በምርጫ እንደሚያስተምርም አስታውቋል።
ወደ ድርጅቱ የውጭ የስራ ዕድልን ለማግኘት የሚመጡ ዜጎች የክፍያ ችግር እንዳይኖርባቸው ከባንኮች እና ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በመነጋገር ሰርተው የሚከፍሉትን ብድር ለማግኘት እየተነጋገሩ መሆናቸውን ስራ አስኪያጁ አቶ ተስፋልደት ፀጋዬ ተናግረዋል።
የውጭ አገር የስራም ሆነ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች የግድ ወደ ተቋሙ በአካል መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሆነው በኦንላይን የተዘጋጀውን የቋንቋ ስልጠና መውሰድ እንዲሁም መረጃዎቻቸውን መመዝገብ እና መሙላት እንደሚችሉም ነው ያነሱት።
የአገር ውስጥ ነጋዴዎችና አምራቾች ከአለም አቀፍ ነጋዴዎችና እና አምራቾች ጋር በመገናኘት የውጭ ገበያ ዕድል ለማግኘት እንዲችሉ የማማከር አገልግሎትም ይሰጣል።
ከዚህ በተጨማሪ ወደ ውጭ አገራት የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ለሚሄዱ ሰዎች የተሻሉ አለም አቀፍ የህክምና ተቋማትን በማጥናት የማማከር አገልግሎት እንደሚሰጥም ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
ወደ ውጭ አገራት በህጋዊ መንገድ የሚሄዱ ዜጎች የተማሩ፣የሰለጠኑ እና በከፊል የሰለጠኑ መሆናቸውንም ነው አቶ ተስፋልደት የተናገሩት።
ድርጅቱ ድምፃዊት ቤተልሔም ሸረፈዲንን ለ2 ዓመታት ከድርጅቱ ጋር ለመስራትም አምባሳደር አድርጎ ተፈራርሟል።
በእስከዳር ግርማ
ነሐሴ 09 ቀን 2016 ዓ.ም
