በነገው እለት በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሁሉም በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ እና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም÷በነገው እለት ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተካለ መርሐ-ግብር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ግርማ አመንቴ ÷ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በሁሉም ክልሎች 8 ሺህ 452 ካርታ የወጣላቸው ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የተዘጋጁት ቦታዎች አጠቃላይ ስፋትም 317 ሺህ 521 ሄክታር መሆኑን ገልጸው÷ለተከላ የሚውሉ ችግኞች በቅርብ ሥፍራ ዝግጁ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት 12 ሰዓት እንደሚከናወን ነው የገለጹት፡፡
ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው÷የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከመጨመር ባለፈ ተጨባጭ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጤት ማስገኘቱን አውስተዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝና ለሌሎች ሀገራት አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የችግኝ ተከላው የደረሰበትን ደረጃ በሚመለከት መረጃው በቴክኖሎጂ ታግዞ ለሕዝብ ተደራሽ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡
በዘንድሮው ዓመት 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን÷ከእነዚህ ውስጥም 56 በመቶ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውና 44 በመቶ ደግሞ የደንና የውበት ችግኞች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ለዚህም 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለተከላ የተዘጋጀ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ ለ1 ሚሊየን ሄክታሩ ካርታ መዘጋጀቱ ነው የተገለጸው፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም
