በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ክለቦች ዞን ማጣሪያ ውድድር የፍፃሜ ጨዋታ ቀን 08:00 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የኢትዮጵያ ተወካዩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኬንያው ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ለ0 በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆኗል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሻምፒዮን ያደረጋቸውን አንድ ግብ ሴናፍ ዋቁማ አስቆጥራለች።
ሦስት ጊዜ ፍፃሜ በመድረስ ብቸኛ ቡድን በመሆን ታሪክ ጽፈው የቆዩት ባንኮቹ በቡድኑ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት በመሆን በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ በማግኘት አዲስ ታሪክ ጽፈዋል።
በሴካፋ ክለቦች ዞን ማጣሪያ ውድድር ላይ አምስት ጨዋታዎችን ያደረገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10 ግቦችን በተጋጣሚው ላይ ማስቆጠር ሲችል 3 ግቦች ብቻ ተቆጥረውበት ያለምንም ሽንፈት ድል በማስመዝገብ ውድድሩን በበላይነት አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፊት ስፍራ ተጫዋቿ ሴናፍ ዋቁማ በስድስት ግቦች የሴካፋ ክለቦች ዞን ማጣርያ ውድድር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አጠናቃለች።
ሴናፍ ዋቁማ ባሳለፍነው የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቋ አይዘነጋም እንዲሁም በአንድ ዓመት ውስጥ በተለያዩ ሁለት ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቅ ችላለች።
በቀጣይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል በካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።
በጋዲሳ መገርሳ
ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም
