በአዲስ አበባ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩ 41 ባቡሮች መካከል አሁን እየሰሩ ያሉት 15ቱ ብቻ መሆናቸው ተነግሯል።
በቂ የመለዋወጫ እቃ አለመኖር እንዲሁም የተበላሹ ባቡሮች የሚጠገኑበት ጋራዥ ባለመኖሩ ምክንያት አብዛኛዎቹ ባቡሮች እንዲቆሙ ምክንያት መሆኑን ነው የተነገረው።
ከጣበያችን ኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የጥናትና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወርቁ ደስታ እንደተናገሩት ከጊዜ ወደ ጊዜ ባቡሮቹ አገልግሎት አሰጣጣቸው እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረው እንደተጠበቀው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም ብለዋል።
አሁን ላይ በከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ባቡሮች 15 ብቻ እንደሆኑም ነው የተናገሩት።
ተበላሽተው የቆሙት ባቡሮች ከዚህ በፊት የአንዱን እቃ ወደ ሌላው በማተካካት አገልግሎት እንዲሰጡ ሲደረግ እንደነበረም ነው አቶ ወርቁ የነገሩን።
አሁን ላይ መንግስት ዘርፉን ለማዘመን የተለያዩ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ያሉት ሀላፊው የከተማው የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መጠቀም የግድ ነው ብለዋል።
ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም
