የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2016 ዓ.ም በአከናወናቸው ቁልፍ ሕገ መንግስታዊ ተግባራት፤ በሕግ አወጣጥ፣ በክትትልና ቁጥጥር እና በውክልና ሥራዎች ለማህበራዊ ፣ ለኢኮኖሚ ልማት መስፋፋት፣ ለሀገር ሠላምና ለዜጎች ብልፅግና መረጋገጥ መሠረት ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን በጥልቀት መርምሮ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጧል፡፡
በፓርላማ ዲፕሎማሲ መስክም የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ መርሆች በመከተል የሀገራችንን እውነተኛ ገፅታ ለውጭው ዓለም ለማስተዋወቅና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ለመደገፍ የሚያስችሉ ውጤታማ ውሳኔዋችን ማሳለፉንም አስታውሷል፡፡
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛው ዓመት የሥራ ዘመኑን አጠናቆ እነሆ በ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን በይፋ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እገኛለሁም ብሏል፡፡
ምክር ቤቱ ባሳለፋቸው የሥራ ዘመናት ያስመዘገባቸውን መልካም ውጤቶችና ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስቀጠል በ2017 አዲስ ዓመት የሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ይበልጥ ምላሽ እንዲያገኙ ፣ የዜጎች የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል፣ ለሕዝቦች አብሮነት እና ዘላቂ ሰላም ፣ ለሀገር አንድነትና ሉዑላዊነት መፅናት ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በትጋትና በቁርጠኝነት የሚወጣ ይሆናል ነው ያለው፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ ሙሉ የትግበራ ሂደት እንዲሳካ ምክር ቤቱ ለምክክር ኮሚሽኑ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የሕዝብ አብሮነትን፤ የሀገር አንድነትንና ሉዑላዊነትን የሚፈታተኑ ከፋፋይ ትርክቶችን አምርረን በመታገል ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጳጉሜ 05 ቀን 2016 ዓ.ም
