በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በ2016 በነበረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ምክንያት 37 ሰዎች በጎርፍ ተወስደዋል ተባለ፡፡

በዞኑ እስከ ሀምሌ 11 የነበረው የዝናብ ስርጭት የተመጣጠነ ቢሆንም ከሀምሌ 11 እስከ መስከረም 6 የነበረው የዝናብ ስርጭት ግን ከፍተኛ በመሆኑ በጎርፍ የተወሰዱ ሰዎች ቁጥር 37 ደርሷል ሲል የዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን አስታውቋል፡፡

እንዲሁም 7 መቶ 31 እንስሳት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በደራሽ ጎርፍ መወሰዳቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በ2016 የክረምት ወቅት የዝናብ ስርጭት ከተለመደው ወጣ ያለ፤ በመጠኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደነበር አንስተዋል፡፡

2 መቶ 77 የሚሆኑ የአርሷ አደር መኖሪያ ቤቶች በመሬት መንሸራተት እና በጎርፍ አደጋ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡

በሁሉም ወረዳ በሚባል ደረጃ ደግሞ የወንዝ ዳርቻን ተከትለው የተሰሩ የመስኖ መሰረተ ልማቶች የጎርፍ አደጋ እንዳጋጠማቸው እና 8 ሺ 3 መቶ 62 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ የበቀለ ሰብል ምርት እንዳይሰጥ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

አንዳንድ ቦታ ላይ መሬቱ ለሚቀጥለውም አመት ለእርሻ አገልግሎት ለመስጠት የማይችልበት ሁኔታ ላይ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡

ተጋላጭ ለሆኑ አርሶ አደሮችም የደረሰባቸውን ጉዳት በመመልከት መልሶ ለማቋቋም ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል እርዳታ ቢያደርግ የሚል ጥሪያቸውን አቶ ምህረት አስተላልፈዋል፡፡

ሐመረ ፍሬዉ

መስከረም 20  ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *