የ32 ሀገራት መሪዎች ተሰብስበው በመምከር የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሰረቱበት ታሪካዊው “አፍሪካ አዳራሽ” እድሳት ሲደረግለት ቆይቶ ዛሬ ይመረቃል።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አዳራሹን በይፋ ይመርቁታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
እድሳቱ ከተመድ ጠቅላላ ጉባዔ በተገኘ 57 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ መከናወኑ ተገልጿል።
እድሳቱ ታሪካዊና ባህላዊ የኪነ ሕንፃ ይዘቶችን ጠብቆ የተከናወነ ሲሆን፤ ሕንፃው እንደ ኒው ዮርክ እና ጄኔቫ ቢሮዎች ሁሉ ቋሚ ዓውደ ርዕይና አባል ሀገራት ልዩ ሁነቶችን የሚያዘጋጁበት ስፍራ እንደተዘጋጀለትም ተጠቁሟል።
‘የአፍሪካ አዳራሽ’ የተሰኘው ሕንጻ እኤአ በ1963 የ32 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መክረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሰረቱበት ታሪካዊ አዳራሽ ነው።
የመጀመሪያውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባዔ ለማስተናገድ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ትዕዛዝ በፍጥነት የተገነባው ይህ ታሪካዊ አዳራሽ የአፍሪካውያን ቅርስ ነው።
በተለይም እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በአዳራሹ መስኮቶች ላይ የሳሏቸው የመስታዋት ስዕሎች÷ የአፍሪካን የትናንት ጭቆና እና መጻኢ ተስፋ አመላካች እንደሆኑ ይነገራል።
የአፍሪካ አዳራሽ በኋላ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መስሪያ ቤት በችሮታ ተሰጥቷል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም
