ጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የዘንድሮ የፓን አፍሪካ “ሳውቦና” ጉባኤ፤ አፍሪካ በምታደርገው ጉዞ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና አመራር በምን መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ ምክክር ተደርጎበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን እንዴት ማንፀባረቅ ፣ ማሰብ እና ማቀድ ይቻላል በሚለው ላይም መክሯል።
ጉባኤው ሴቶች ፍትሃዊ እና አካታች አመራርን እንዴት መገንባት እና ማበርታት አለባቸው የሚለውንም ያሳየ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በጉባኤው የሴቶች መብት ተሟጋቾች ፣ በአመራር ደረጃ ያሉ ሴቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ዓለም አቀፍ መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ሀላፊዎች ተሳታፊ ሆነውበታል።
በብዛት የህዝባቸው ቁጥር ወጣት ከሆኑ 20 አገራት መካከል 18ቱ በአፍሪካ የሚገኙ ቢሆንም፤ በወጣቶች አመራር ላይ ግን አለመሰራቱ ተነስቷል።
በ2030 በአፍሪካ ከሚኖሩ ዜጎች 42 በመቶው ወጣት እንደሚሆንም በጉባኤው ተገልጿል።
ወጣቶች እና ሴቶችን ወደ መሪነት ማምጣት እንደሚገባም ነው የተገለጸው።
ከአፍሪካ ሩዋንዳ 63 በመቶ የሚሆነው የመንግስት ስልጣን በሴቶች የተያዘ መሆኑ ሲገለፅ፤ አገሪቱን ለሴቶች የመሪነትን ድርሻ በመስጠት በመጀመሪያ ደረጃ እንድትቀመጥ አድርጓታል።
ይህንን ጉባኤ ” አኪና ማማ ዋ አፍሪካ” የተሰኘ በሴቶች ላይ የሚሰራ ድርጅት ከአፍሪካ ልማት እና ኮሚኒኬሽን እና ከታንዛኒያ የፆታ ጉዳይ ትስስር ጋር በጋራ አዘጋጅተውታል።
እስከዳር ግርማ
ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም
