ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ የጥቅምት ወር ክፍያን ታሳቢ በማድረግ እንደሚከፈል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኮሚሽነሩ በማህበራዊ ትስስት ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ “የተፈቀደው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ ዘግይቷል፣ ቀርቷል የሚሉ ሃሳቦች እየተራመዱ ነው። በሲቪል ሰርቪስ በኩል የሚለቀቁ መረጃዎች ኦፊሴላዊና የሚተገበሩ መሆኑን መተማመን ጥሩ ነው።” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ ቀደም ሲል የመንግሥት ሰራተኞችን የደመወዝ ስኬል በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚናፈሱ አሳሳች ወሬዎች ማህረሰቡ እንዳይሳሳት መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የተጨማሪ ክፍያ በጀቱን ለሚመለከታቸው ተቋማት መፍቀዱን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ “በእኛ መስሪያ ቤትም በኩል የተስተካከለውን የጥቅምት ወር ደመወዝ ተከፍሏል። ሌሎችም እንደዚሁ የከፈሉ አሉ” ብለዋል።
የቀሩት ተቋማት ደግሞ ማስተካከያውን ለማድረግ የማጥራት ሥራ እየሰሩ ሊሆን እንደሚችል ያመላከቱም ሲሆን፤ “እነዚያም ዝግጅታቸውን ሲያጠናቅቁ የተስተካከለው የጥቅምት ወር ክፍያ ታሳቢ በማድረግ የሚከፍሉ ይሆናል።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ ጥቅምት 09/2017 ዓ. ም በሰጡት ማብራሪያ አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው ነበር።
በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፤ ለደሞዝ ጭማሪው 91 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጸው፤ ክፍያው ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም
