ሚኒስክ እንደ ሃቫና


አሌግዛንደር ሉኬሼንኮም እንደ ካስትሮ የሆኑበት ዘመን እየተፈጠረ ነዉ፡፡

የኩባዉን የሚሳኤል ቀዉስ የወለደዉ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ነዉ

የቤላሩሱን የኒኩለር ጣጣ የፈበረከዉ ደግሞ የኔቶ መስፋፋትና የዩክሬኑ ፍጅት ነዉ፡፡

ፑቲን ከሰሞኑ ወዳጃቸዉ የቤለሩሱን ፕሬዝዳንት አሌግዛንደር ሉካሼንኮን እንዴት ሰነበትክ ሊሉ ወደ ሚኒስክ አቅንተዉ ነበር፡፡
ሰዉየዉ ሰሜን ኮሪያ ያደረጉትን በቤላሩስም ደግመዉታል፡፡

ዛሬ አሉ የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌግዛነደር ሉኬሼንኮ ዛሬ እነ አሜሪካ የሚያወሩት ኦሬንሺክ የተሰኘዉን የሩሲያን ጨራሽ ሚሳኤል ሊታጠቁ ይችላሉ የሚል ነዉ፡፡
ግን እኮ የኒዉኩለር ጦር መሳሪያን መታጠቃችንን የዘነጉት ይመስላል ብለዋል፡፡
በዩክሬንና በፖላንድ የተከበበችዉ አገረ ቤላሩስ ግን ደግሞ አመሏን አሳምራ ለፑቲን ተገዢ በመሆኗ ኒዉክሌር ጦር መሳሪያን በደጇ የደቀነችዉን ብዙዎች በቀዝቃዘዉ ጦረነት ዘመን ከነበረችዉ ኩባ ጋር በርካቶች ያመሳስሏታል፡፡

ያኔከሁለተኛዉ የአለም ጦርነት በቅጡ ያላገገመችዉ አለም ከአስፈሪዉ የኒዉክሌር ጦርነት አፋፍ ላይ ደርሳ ነበር፡፡
በኩባዉ የሚሳኤል ቀዉስ ምክነያት መሆኑ ነዉ፡

የሶቭየትሕብረት ኒዉክሌር አወንጫፊ ሚሳዬሎች ቀስታቸዉን ነጩ ቤተመንግስት ደግነዉ ኩባ ምድር ተጠመዱ።
በጃፓኖቹ ከተሞች ሔሮሺማና ናጋሳኪ ዘርማንዘር አጥፊዉን ቦምብ በማፈንዳት የታወቁት የሜሪካ ኑክሌር ጣይ ጄቶች ለበረራ ተዘጋጁ።

የሁለቱ ሐገራት ዘመናይ የጦር መርከቦች ያንዱ ወደ ተቃራኒዉ ይቀዝፉ ጀመር፡፡
የሁለቱ አገራት መሪዎች ብልጠት ታክሎበት የተፈራዉ የኒዉክሌር ጦርነት በርግጥ አልተጫረም፡፡

አሁንም አዉሮፓ ብቻም ሳትሆን አለም በእንቆቅልሹ የዩክሬን ጦርነት እንቅልፏን አታለች፡፡

የአወዛጋቢዉ የዶናልድ ትራምፕ የሰላም እቅድን በጉጉት የሚጠባበቁ አገራት ቁጥርም የት የሌሌ ነዉ፡፡

ግን ደግሞ የጦር መሳሪያ እሽቅድምድሙና ፉከራዉ ዛሬም ሃያላኑ ጎራ ለይተዉ ዛቻና ማስፈራሪያቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ፡፡

ለአመታት ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተነጥላ የቆየችዉ ምስጢራዊቷ ሰሜን ኮሪያን አግባብተዉ ታማኝ ወዳጅ ያደረጉት የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወታደሮቿን በዩክሬን ድንበር እስከማስፈር አድርገዋል፡፡

የምእራቡ አለም ሰዎች የምድረ አዉሮፓዉ አምባገነን መሪ አያሉየሚጠሯቸዉን የቤላሩሱን አለቃ አሌግዛንደር ሉኬሼንኮንም እንካ ለክፉ ቀን ይሆንሃል ብለዉ አዉዳሚዉን የኒዉክሌር ጦር መሳሪያ በሚኒስክ ደጃፍ ላይ አቁመዉላቸቨዋል፡፡

አሁን ሞስኮ ጫፏን ስትነካ ፕዮንግያንግ በቀጥታ እንደምትሳተፍ ኪምና ፑቲን ለአለም እንዳሳወቁት ሁሉ ሚኒስክም የሞስኮን መጠቃት ቁጭ ብላ እንደማትመለከት በግልጽ አስታዉቃለች፡፡

በርግጥ የቀድሞዉ የሶቪየት ህብረት አባል የነበረችዉ አገረ ቤላሩስ ፀባይዋን አሳምራ ከክሪሚሊን ከሞስኮ ወንዝ የሚንቆረቆረዉን ወተደራዊ ድጋፍ ስትምግ ያሁኑ አዲስ አይደለም፡፡

ግን ሰሞነኛዉ የሚኒስክና የክሪሚሊን አለቆች ስምምነት የምእራቡ አለምን ሰዎች እንቀልፍ ነስቷል ይላል የአርቲ ኒዉስ ዘገባ፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ፑቲንና ሉኬሼንኮ ከመከሩባቸዉ ጉዳዮች መካከል በቅርቡ ሩሲያ ይፋ ያደረገችዉን ጨራሹን ኦሬሽኒክ የተሰኘዉን ሚሳኤል በቤላሩስ ምድር እናጠምዳለን በማለታቸዉ ነዉ፡፡

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ‘ኦሬሽኒክ’ የተባለውን የመካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳይል በ2025 መጨረሻ ወደ ቤላሩስ ልትልክ ትችላለች ሲሉ ተናግረዋል።

ሚሳይሉ እጅግ ፈጣን እና አሁን ባላት የአየር መከላከያ ስርአት ማክሸፍ አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጻለች።

ሩሲያ እንደገለጸችው ሚሳይሉ የአሜሪካን ምዕራባዊ ክፍል እና አውሮፓው ውስጥ ያሉ የትኞቹንም ኢላማዎችን የመምታት አቅም አለው።

ከሩሲያ ጀርመን ለመድረስ 14 ደቂቃ ብቻ እንደሚበቃው የተነገረለት “ኦሬሽኒክ” በ40 ደቂቃዎች ውስጥ በአሜሪካ ያሉ ኢላማዎችን መምታት እንደሚችል ተገልጿል።
የሚኒስኩ ሰዉ ግን ይሄ ለምን ይገርማችኋል ከዚህ መሳሪያ በእጅጉን የላቀዉ አዉዳሚዉ የኒዉክለር ጦር መሳሪያ እኮ ምስጋና ለፑቲን ይግባና በእጃችን ይገኛል ነዉ ያሉት፡፡

ይህንንም ተከትሎ የአዉሮፓ አገራት ከፍተኛ ስጋት መዉደቃቸዉ እየተነገረ ነዉ፡፡
ቤላሩስን ለለፉት 30 አመታት እያስተዳደሩ የሚገኙት አሌግዛንደር ሉኬሼንኮ ግን የኒዉክለር ጦር መሳሪያን በእጃችን ስላለ ብቻ የምንተኩሰዉ ሳይሆን ለክፉ ቀን የሚዉል ነዉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደምትረዱት ከሄሮሺማና ናጋሳኪ ፍጅት በኋላ የትኛዉም አገር የኒኩለር ቁልፉን አልተጫነም ስለዚህ ለመተኮስ የምንቸኩልበት ነገር የለም ሲሉ ሉኬሼን ተደምጠዋል፡፡

የሩሲያ የቅርብ አጋር የሆነችው ቤላሩስ ጦሯን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷ የሚታወስ ነዉ።

የዩክሬን ድሮኖቸ የአየር ክልሏን እንደጣሱባት የገለጸችው ቤላሩስ ተጨማሪ ወታደሮችን ከዩክሬን ወደምትዋሰንበት ድንበር ልካለች።

ኔቶን ወደ ሩሲያ አፍንጫ እያስፋፋች ያለችዉ ጦሯንም ወደ ሩማኒያ የመሳሰሉ የአዉሮፓ አገራት እያሰፈረች ያላችዉ አገር አሜሪካ ከ60 አመት በኋላ ሉኬሸንኮ ካስትሮን ሚኒስክም ሃቫናን ሆነዉባት ግራ ተጋብታለች፡፡

አባቱ መረቀ

ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *