ዉሳኔዉ የተሻለ ነዉ ብለን እናምናለን-የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፤ መንግሥት ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባውን ነዳጅ “ለመቀነስ እየተሰራ” በመሆኑ ለአዲስ ማደያዎች ነዳጅ ላለማቅረብ መወሰኑን አስታዉቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጣቢያችን ያነጋገራቸዉ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር የቦርድ አባል አቶ ደሳለኝ አበባየሁ፤ በአገሪቱ ያለዉ ማደያ በአግባቡ የሚፈልገዉን ያህል አቅርቦት እያገኘ ባለመሆኑ ይህ ዉሳኔ የተሻለ ነዉ ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡

ወደ ክፍለ አገር ወጣ ሲባል በአንድ ከተማ ላይ ለከተማዉ ከሚያስፈልገዉ በላይ ማደያ ነዉ ያለዉ የሚሉት አቶ ደሳለኝ፤ በቂ የነዳጅ አቅርቦት ግን የለዉም ሲሉ ነግረዉናል፡፡

አንድ ሰዉ ከ20 እና 30 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አዉጥቶ ማደያ ገንብቶ ወደ ስራ ልግባ ቢል አቅርቦት ከሌለ ምንም ማድረግ አይችልም ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ቴክኖሎጂዉም ወደ ኤሌክትሪክ እየዞረ በቤንዚን እና ናፍጣ የሚሰሩ መኪኖች እየገቡ ባለመሆናቸዉ ፤ ዉሳኔዉ አስቀድሞ ሰዉ ሳይጎዳ በጊዜ እንዲያዉቅ ያደርገዋል ነዉ ያሉት፡፡

የነዳጅ እጥረቱን በተመለከተ ላቀረብንላቸዉ ጥያቄ፤ መንግስት የኤሌክትሪል መኪኖችን ለማስገባት በሰጠዉ አቅጣጫ መሰረት እየተንቀሳቀሰ ነዉ እኛም የምንደግፈዉ እሱን ነዉ ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

እንደ አገርም የሚጠቅመን እሱ ነዉ ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ያለውን የነዳጅ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ከውጭ ሀገር ነዳጅ የማስገባት እና ለአከፋፋይ ኩባንያዎች የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፤ ይህንን ውሳኔውን ያስታወቀው ሰኞ ሕዳር 30/2017 ዓ.ም. ለነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን በጻፈው ደብዳቤ ነው።

እሰከዳር ግርማ

ታህሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *