የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “የላቀ አገልግሎት ደስተኛ ደንበኛ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ የደንበኞች አገልግሎት ወር በይፋ ዛሬ አስጀምሯል።
መርሐ ግብሩ በባንኩ ባሉ ሁሉም ቅንጫፎች በመላው ኢትዮጵያ በድምቀት በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ሰምተናል፡፡
ከታህሳስ 24 እስከ ጥር 25 ለአንድ ወር በሚቆየው በዚህ መርሐ ግብር በባንኩ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከደንበኞች ጋር ውይይት፣ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ አወደ ርዕይ እና ለደንበኞች ምስጋና የሚቀርብበት መሆኑን ተገልጿል።
ለአራት ሳምንት በሚቆየው ዝግጅት የደም ልገሳ፣ ማስ ስፖርት፣ የንግድ ትርኢት፣ የተለያዩ ውይይቶችና እና ሌሎች ማህበራዊ ክንውኖች እንደሚኖር ነው የተነገረው።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ”ደንበኞቻችን ስለምትተማመኑብን እጅግ እናመሰግናለን ፤ባንካችን ለደረሰበት ስኬት ላደረጋችሁት አስተዋፅኦ ሁሉ ክብር ይገባችኋል” ብለዋል፡፡
ባንኩ ለደንበኞች አስተማማኝና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ በዚህም በቴክሎጂ ዘርፍ የደንበኞች የዲጂታል አገልግሎት 81 በመቶ መድረሱን አንስተዋል።
በሌላ በኩል የባንኩ ተቀማጭ ሀብት 1 ነጥብ 97 ትሪሊየን ብር መድርሱም ነው የተገለጸው። በተጨማሪ ያለው ካፒታል 131 ቢሊየን ካፒታል መድረሱን ጠቁመዋል።
የደንበኞቹ ቁጥር 45 ሚሊየን መድረሱን እና በቀጣይ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት እንደሚሰራ ፕሬዝዳነቱ ተናረዋል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ እና የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።
ጋዲሳ መገርሳ
ታኀሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም
