በሶማሊያ በአዲሱ የአፍሪቃ ሕብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ተልእኮ ውስጥ ኢትዮጵያም እንድትካተት መፈለጓን ይፋ አደረገች።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ኦማር ባልሳድ በሀገራቸው በኩል የውሳኔ ለውጥ መኖሩን አመልክተው፤ ከዚህ ውሳኔ አስቀድሞ ሌሎች ሃገራት የወታደር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በመጠየቃቸው አዳጋች ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ግን አልሸሸጉም።
እሳቸው እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ በዚህ የሕብረቱ የሶማሊያ ተልእኮ ውስጥ እንዳትካተት እንቅፋት የነበረው ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የግባቢያ ሰነድ ነው።
እንደእሳቸው ገለጻም «ያ ርዕሰ ጉዳይ መፍትሄ አግኝቷል»። አያይዘውም አሁን ዋና ፈተና የሆነባቸው፤ የሚፈለገው የወታደር መጠን በአብዛኛው በሌሎች ሃገራት በመሸፈኑ፤ ቀሪውን ትንሽ ቁጥር የማከፋፈሉ ጉዳይ ነው።
ለዚህም መፍትሄ ለማግኘት በንቃት እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያን መፈራረም ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከግዛቷ እንዲወጡ ደጋግማ መጠየቋን ተከትሎ ግብፅ ፈጠን ብላ በዚህ ተልዕኮ ሥር ወታደሮቿን ለማሰማራት ዝግጁ መሆኗን አሳውቃ፤ ከመቃዲሹም ይሁንታ ማግኘቷ አይዘነጋም።
በአዲሱ የአፍሪቃ ሕብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ሥር ወታደሮችን የሚያሰማሩት ሃገራት እስካሁን ዝርዝራቸው ይፋ አልሆነም።
አዲስ አበባ እና መቅዲሹ ቅርቡ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት አርግበው የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን የማሻሻል ሂደት መጀመራቸው እየተነገረ ነው።
የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ በቅርቡ በሶማሊያ አምባሳደሯን ወደ መቃዲሹ እንደምትልክ የገለጹ ሲሆን፤ ሶማሊያም እንዲሁ አዲስ አምባሳደር ወደ አዲስ አበባ ትልካለች ብለዋል።
ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም
