እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ

ለአስራ አምስት ወራት የተካሄደውን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል።

በኳታር እና በአሜሪካ አሸማጋይነት በተደረሰው ስምምነት መሠረት በሐማስ የታገቱ እስራኤላውያን የሚለቀቁ ሲሆን እስራኤልም ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼኽ መሐመድ ቢን አብዱል ራሕማን አል ታሕኒ እንዳሉት ስምምነቱ በእስራኤል ካቢኔ ከፀደቀ የፊታችን ዕሑድ ይተገበራል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስምምነቱ “በጋዛ ግጭት ያስቆማል፣ የሰብአዊ እርዳታ ለንጹሃን ፍልስጤማውያን ዜጎች ያደርሳል፣ ታጋቾችን አስለቅቆ ከቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ ያስችላል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የስምምነቱ የመጨረሻ ዝርዝሮች አሁንም እየታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባይደን ስምምነቱን ወደፊት በማምጣታቸው ኔታንያሁ አመስግነዋል።

የሐማስ መሪ ካሕሊል አል-ሐያ ስምምነቱ የፍልስጤም አይበገሬነት ውጤት ነው ብለዋል።
ፍልስጤማውያን እና የታጋቾች ቤተሰቦች በዜናው ተደስተዋል።

“ጥሩ ዜና ቢሆንም ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውን ሰዎችም አንረሳም። በጦርነቱ የሞቱ ንጹሃንንም አንዘነጋም። ጦርነቱ ከዚህ ቀድሞም መቆም ነበረበት” ብለዋል ባይደን።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ለስምምነቱ ሚና እንደነበራቸው ባይደን ጠቁመዋል።

በሁለቱም ወገኖች ላይ ጫና በማሳደር ስምምነቱ እንዲፈረም ትራምፕ ማስቻላቸው ተገልጿል፡፡

ስምምነቱ መደረጉን ከኳታር እና ጆ ባይደን ጽህፈት ቤት ቀድመው ይፋ ካደረጉት መካከል ትራምፕ አንዱ ናቸው። ስምምነቱን “ታላቅ” ሲሉም ገልጸዋል።

“በኅዳር ምርጫ አስደናቂ ድል በማግኘታችን የመጣ ስምምነት ነው” ብለዋል ትራምፕ።

ኔታንያሁም ትራምፕ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ባደረጉት ጫና አመስግነዋቸዋል።

ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *