ኬንያ “በፀጥታ ስጋት” ሳቢያ ከሊቢያ እና ሶማሊያ በስተቀር ለአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች የጉዞ ፍቃድ ቅድመ ሁኔታን መሰረዟን አስታውቃለች።
ካቢኔው እርምጃው “ክልላዊ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዲሁም በአህጉሪቱ የሚደረጉ ጉዞዎችን የማቃለል” ጥረት አካል ነው ብሏል።
ከዚህ ቀደም ኬንያ ወደ አገሯ የሚገቡ ጎብኚዎች በኤሌክትሮኒክስ ለጉዞ ፍቃድ እንዲያመለክቱ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣ ነበር፤ ይህንን አሰራር ብዙዎች “በሌላ ስም ቪዛ” መጠየቅ ነዉ በማለት ሲተቹት ቆይተዋል፡፡
የተሻሻለው ፖሊሲ የአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ዜጎች በኬንያ ለሁለት ወራት እንዲቆዩ የሚፈቅድ ሲሆን፤ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አባል አገራት ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ዜጎች ደግሞ እስከ ስድስት ወራት እንዲቆዩ የሚፈቅድ ነዉ፡፡
መንግሥት የመግቢያ ሂደቶችን የማሳጠር እቅድ እንዳለው ገልጾ፤ ከፍተኛው በ72 ሰአታት የሚያልቅ አሰራርን በማስተዋወቅ አስቸኳይ ፍቃዶችን ለመስጠት ማሰቡን አስታዉቋል፡፡
አሰራሩ ተግባራዊ የሚሆንበት ቀን ባይገለጽም፤ ካቢኔው የተደረገዉ ለዉጥ በሁሉም የኬንያ አየር ማረፊያዎች ለሚገኙ ተጓዦች ተግባራዊ የሚደረግ ነዉ ብሏል፡፡
ኬንያ የደረሰችበት ዉሳኔ በአፍሪካ ዉስጥ የሚደረጉ ጉዞዎችን ለማቃለል በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ ከዚህ ቀደም ጋና እና ሩዋንዳ የጀመሩትን መንገድ የተከተለ ሆኗል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም
