የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን በ6 ወራት ዉስጥ ከ50ሺህ በላይ የትራፊክ ደንብ ተላልፈዉ የተገኙ ዜጎችን መቅጣቱን አስታዉቋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ6 ወራት ጊዜ ዉስጥ መንገዶችን ለእግረኛ ምቹ ማድረጉን እና ከ5መቶ በላይ የተማሪ ትራፊክ ፖሊሶችን ማሰልጠኑንም ገልጿል፡፡
ከ50ሺህ በላይ የትራፊክ ደንብ የተላለፉ ዜጎችን መቅጣቱን እና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎችን መገንባቱን የገለጹት በባለሥልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ዳይሬክተር አቶ ጎይቶም አስፋው ናቸዉ፡፡
ከደንብ ማስከበር ቢሮ ጋር በመሆን 1መቶ19 ሕንፃዎች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃዎችን በመውሰድ የገንዘብ ቅጣት እንዲጣል መደረጉም ተገልጿል፡፡
1መቶ45 ሕንፃዎች የብቃት ማረጋገጫ ወስደው ወደ ሥራ እንዲገቡ እንዲሁም የሕንፃ ሥር ተሽከርከሪ ማቆሚያ ቦታዎቻቸውን ለታለመላቸው ዓላማ እንዲያውሉ ማድረግ መቻሉንም አቶ ጎይቶም ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 84 ትምህርት ቤቶችን በጥናት መለየቱንም ነዉ ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች አከባቢም ከ5መቶ በላይ ረዳት የተማሪ ትራፊክ ፖሊሶችን አሠልጥኖ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ላይ እንዲሰማሩ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
የመንገድ ደህንነት ጽንሰ ሃሳብ በመጀመሪያ ደረጃ (ከ1-8ኛ ክፍል) ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት በ4 የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች እንዲሰጥ በማድረግ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሲደርሱ የነበሩ የትራፊክ አደጋዎችን መከላከል ተችሏል ብለዋል፡፡
እስከዳር ግርማ
ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም
