ጥራታቸዉ ከሚመረቱበት ቦታ ጋር የተገናኙ ምርቶችን ላይ የባለቤትነት መብት ጥበቃ የሚያደርግ ረቂቅ ህግ በመጪዉ በጀት አመት ለፓርላማ ሊቀርብ እንደሆነ ሰምተናል።
በኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ እንደ የሸኖ ቅቤ÷ የሀላባ በርበሬ እንዲሁም የመቀሌ ማር እና የአዳ ጤፍን የመሰሉ፤ ሌሎች ምርቶች የተመረቱበት አካባቢ መጠሪያ የሆነ የምርት ጥራት ይዘት እንዳላቸዉ ይታመናል።
ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዩጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን የማህበረሰብ እዉቀት ዘርፍ ስራ መሪ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ወርቁ ይህን የሚያስፈፅም ኘሮጀክት መተግበሩን ገልፀዋል።
የመልክአ ምድራዊ አመላካች ምርት እሳቤ አንዱ የአእምሮአዊ ንብረት ወሳኝ ዘርፍ ነዉ ተብሏል።
በኢትዩጵያ የምርቶችን ጥራት የሚገለፅበት አንዱ ዘዴ የምርት ቦታዎች መሆናቸዉን ያነሱት አቶ ታደሰ አካባቢዎቹ ባላቸዉ ፀጋ እና ማህበረሰቡ ባለዉ እዉቀት ምርቶቹ ያላቸዉን ዝና ለመጠበቅ የሚዘጋጅ የህግ ማእቀፍ መሆኑንም አንስተዋል።
የዚህ ረቂቅ ህግ ዋና አላማ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የግብርና መር ኢኮኖሚ ለሚከተሉ ሀገራት ለአምራቾች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እና የንግድ ዉድድር እንዲኖራቸዉ ያደርጋል ተብሏል።
ይህንን በተመለከተ የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ጋር በመሆን የግብአት የማሰባሰብ ስራዉን ማጠናቀቅ መቻሉን ገልፆል።
የዘርፉ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ወርቁ በቀጣይ በሚኖሩ ሁለት አመታት ህግ ሆኖ ፀድቆ ይወጣል የሚል ተስፋ አለ ብለዋል።
ሆኖም ስለ አእምሮአዊ ንብረት ጥበቃ በቂ፤ ምልከታ በማህበረሰቡ ዘንድ ስለሌለ የግንዛቤ ስራዎችን በተከታታይነት መስራት እንደሚጠበቅ አያይዘዉ ገልፀዋል።
ቁምነገር አየለ
ጥር 20 ቀን 2017 ዓ.ም
