የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በኩባ በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ መቀመጫ ጓንታናሞ ቤይ እስከ 30 ሺህ ሰዎች የሚይዝ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል እንዲገነባ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ተዘግቧል፡፡
ይህ ማዕከል ጓንታናሞ ቤይ ከሚገኘው ወታደራዊ እስር የተለየ ማቆያ እንደሚሆን ገልጸዋል ተብሏል፡፡
ማዕከሉ መቼ እንደሚገነባና ምን ያህል እንደሚያስወጣ አልታወቀም።
“አስከፊ የሆኑትና አሜሪካን የሚያሰጉት ሕገ ወጥ ስደተኞችን የሚይዝ ይሆናል” ብለዋል ትራምፕ።
በጓንታናሞ ቤይ ስደተኞችን ማቆየት ከዚህ በፊትም የሚደረግ ነበር። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድርጊቱን ይተቻሉ።
ትራምፕ በስደተኞች ጉዳይ የሾሟቸው ቶም ሆማን እንዳሉት የአገሪቱ የስደተኞችና ጉምሩክ ተቋም አይስ እየተጠቀመበት ያለው ማዕከል ማስፋፊያ ይደረግበታል።
ስደተኞች በአሜሪካ የባሕር ኃይል ተይዘው ወደማቆያው በቀጥታ እንደሚወሰዱና “ከፍተኛ” እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።
የኩባ መንግሥት የትራምፕን ዕቅድ ኮንኗል። አሜሪካ “በይዞታ” በተቆጣጠረችው መሬት በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን እያገተችና እያሰቃየች ነው ሲልም ከሷል።
‘ላኪን ሪሌይ አክት’ የተባለውን ሕግ ትራምፕ ከፈረሙ በኋላ ነው ውሳኔውን ያሳለፉት።
ሰነድ አልባ ስደተኞች በስርቆት ወይም ነውጥ ከታሰሩ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ሆነው ይከታተላሉ።
ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም
