የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ለአምስት ዓመታት ሲመሩ የነበሩት ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) ጊዜያቸውን ጨርሰው በፓርላማ ከተሰናበቱ ከአምስት ወራት በኋላ ዛሬ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን ለስድስት ዓመታት የካቤኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው የሰሩትን አቶ ብርሃኑ አዴሎ ኮሚሽኑን እንዲመሩ በፓርላማ ተሾሙ።
ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ኢሰመኮ፤ ለሰብዓዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የመስራት ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ሲሆን፣ ዳንኤል (ዶ/ር) ተቋሙን በመሩባቸው አምስት ዓመታት ኃላፊነታቸውን በብቃት የተወጡ ቢሆንም በሕግ እንዲጠየቁ ጭምር ከፓርላማ አንዳንድ አባሎች የቀረበባቸውን ጫና ተቋቁመው ተቋሙ ገለልተኛ በመሆን ለመስራት የሚያስችለውን አሠራር መዘርጋታቸው ይነገራል፡፡
አቶ ብርሃኑ ተቋሙ ላለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሲተገብር የቆየውን አሰራር ማስቀጠል እንደሚገባቸው ከወዲሁ ስየተነገረ ነው፡፤
በ2012 ዓ.ም. የተሻሻለው የኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ተቋሙን በዋና ኮሚሽነርነት፣ በምክትል ዋና ኮሚሽነርነት እና በዘርፍ ኮሚሽነርነት የሚያገለግሉ ኃላፊዎች በተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ ይደነግጋል።
አቶ ብርሃኑ አዴሎ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተርነት ከተነሱ በኋላ ላለፉት አስር አመታት በግል የሕግ አማካሪነትና ጥብቅና ሥራ ላይ እንደነበሩ ታውቋል፡፡
ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም
